ኢሳይያስ 63 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የአሕዛብ ድል መሆን 1 ከኤዶምያስ፥ ከባሶራ የሚመጣ፥ ልብሱም የቀላ፥ የሚመካ ኀይለኛ፥ አለባበሱም ያማረ፥ ይህ ማን ነው? ስለ ጽድቅ የምከራከር፥ ስለ ማዳንም የምፈርድ እኔ ነኝ። 2 ቀሚስህ ስለ ምን ቀላ? ልብስህስ በወይን መጭመቂያ እንደሚረግጥ ሰው ልብስ ስለ ምን መሰለ? 3 መጭመቂያውን ብቻዬን ረግጫለሁ፤ ከአሕዛብም አንድ ሰው ከእኔ ጋር አልነበረም፤ በቍጣዬም ረገጥኋቸው፤ በመዓቴም ወደ መሬት ጣልጥህዋቸው፤ ደማቸውንም በምድር ላይ አፈሰስሁ፤ ልብሴም ሁሉ በደም ታለለ። 4 የምበቀልበት ቀን ደርሶባቸዋልና፥ የምቤዥበትም ዐመት ደርሶአልና። 5 የሚረዳም እንደሌለ አየሁ፤ የሚያግዝም እንደሌለ ዐወቅሁ፤ ስለዚህ በገዛ ክንዴ አድናቸዋለሁ፤ ቍጣዬም ወደቀችባቸው። 6 በመቅሠፍቴ ረገጥኋቸው፤ ደማቸውንም ወደ ምድር አፈሰስሁት። የእግዚአብሔር ቸርነት ለእስራኤል 7 በስጦታው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቸርነትና የእግዚአብሔርን ምስጋና ዐሰብሁ፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ወገኖች እውነተኛ ፈራጅ ነው፤ እንደ ቸርነቱና እንደ ጽድቁ ብዛትም ይቅርታውን ያመጣልናል። 8 እርሱም፥ “ሕዝቤ ልጆች አይደሉምን? ካልከዱኝስ ከመከራቸው ሁሉ አድናቸዋለሁ” አለ። 9 በመልእክተኛም አይደለም፤ በመልአክም አይደለም፤ እርሱ ራሱ ያድናቸዋል እንጂ። እርሱ ይወዳቸዋልና፥ ይራራላቸዋልምና እርሱ ተቤዣቸው፤ ተቀበላቸውም፤ በዘመናቸውም ሁሉ ለዘለዓለም አከበራቸው። 10 እነርሱ ግን ዐመፁበት፤ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፤ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፤ እርሱም ተዋጋቸው። 11 እርሱም እንዲህ ብሎ የቀደመውን ዘመን ዐሰበ፥ “በበጎቹ እረኛ እጅ ከግብፅ በወጡ ጊዜ መልአኬን በፊታቸው ላክሁ። 12 በሙሴም ቀኝ እጅ ውኃውን ከፈልሁ፤” ውኃውም ተከፍሎ በፊቱ ጸና፤ የዘለዓለም ስምንም አደረገለት። 13 ፈረስ በምድረ በዳ እንደሚያልፍ፥ በቀላይ ውስጥ አሳለፋቸው፥ እነርሱም አልደከሙም። 14 ወደ ሸለቆ እንደሚወርዱ ከብቶች፥ እንዲሁ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ዕረፍት አመጣቸው፤ እንዲሁም ለራስህ የከበረ ስምን ታደርግ ዘንድ ሕዝብህን መራህ። ምሕረትንና ርዳታን ለመግኘት የቀረበ ጸሎት 15 ከሰማይ ተመለስ፤ ከቅድስናህና ከክብርህ ማደሪያም ተመልከት፤ ቅንአትህና ኀይልህስ ወዴት ነው? የቸርነትህና የይቅርታህ ብዛት ወዴት ነው? ቸል ብለሃልና። 16 አንተ አባታችን ነህ፤ አብርሃም ግን አላወቀንም፤ እስራኤልም አልተገነዘበንም፤ ነገር ግን አንተ አባታችን አድነን፤ ስምህም ለዘለዓለም በእኛ ላይ ነው። 17 አቤቱ፥ ከመንገድህ ለምን አሳትኸን? እንዳንፈራህም ልባችንን ለምን አጸናህብን? ስለ ባሪያዎችህ ስለ ርስትህ ነገዶች ተመለስ፤ 18 በተቀደሰው ተራራህ ከርስትህ ጥቂት ክፍል እናገኝ ዘንድ። 19 ከጥንት እንዳልገዛኸን ስምህም በእኛ ላይ እንዳልተጠራ ሆነናልና። |