ኢሳይያስ 59 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሕዝቡ ኀጢአት እንደ ተወገዘ 1 በውኑ፥ የእግዚአብሔር እጅ ማዳን አትችልምን? ጆሮውስ አይሰማምን? 2 ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በእግዚአብሔር መካከል ለይታለች፤ ይቅርም እንዳይላችሁ ኀጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል። 3 እጃችሁ በደም ጣታችሁም በኀጢአት ተሞልትዋል፤ ከንፈራችሁም ዐመፅን ተናግሮአል፤ ምላሳችሁም ኀጢአትን አሰምቶአል። 4 ጽድቅን የሚናገር በእውነትም የሚፈርድ የለም፤ በከንቱ ነገር ታምነዋል፤ የማይጠቅማቸውንም ተናግረዋል፤ ኀጢአትን ፀንሰዋል፤ በደልንም ወልደዋል። 5 የእባብን ዕንቍላል ቀፈቀፉ፤ የሸረሪትንም ድር አደሩ፤ እንቁላላቸውንም የሚበላ ሰው ፈጥኖ ይሞታል፤ እንቍላሉም ሲሰበር እባብ ይወጣል። 6 የሸረሪቶች ድር ልብስ አይሆንም፤ በሥራቸውም ራሳቸውን አያለብሱም፤ ሥራቸው የግፍ ሥራ ነውና። 7 እግሮቻቸውም ለተንኮል ይሮጣሉ፤ ደምን ለማፍሰስም ይፈጥናሉ፤ ሰውን ለመግደል ይመክራሉ፤ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ በመንገዳቸው አለ። 8 የሰላምን መንገድ አያውቁም፤ በመንገዳቸውም ፍርድ የለም፤ የሚሄዱበትም መንገድ ጠማማ ነው፤ ሰላምንም አያውቁም። 9 ስለዚህ ፍርድ ከእነርሱ ዘንድ ርቆአል፤ ጽድቅም አላገኛቸውም፤ ብርሃንን ሲጠባበቁ ብርሃናቸው ጨለማ ሆነባቸው፤ ብርሃንንም ሲጠባበቁ በጨለማ ሄዱ፤ 10 እንደ ዕውሮች ወደ ቅጥሩ ተርመሰመሱ፤ ዐይንም እንደሌላቸው ተርመሰመሱ፤ በቀትርም ጊዜ በመንፈቀ ሌሊት እንዳለ ሰው ተሰናከሉ፤ እንደ ሙታንም ይጨነቃሉ። 11 እንደ ድብና እንደ ርግብ በአንድነት ይሄዳሉ፤ ፍርድን እንጠባበቅ ነበር፤ መዳንም የለም፤ ከእኛም ርቆአል። 12 ዐመፃችን በአንተ ፊት በዝቶአልና፥ ኀጢአታችንም መስክሮብናልና፥ ዐመፃችን ከእኛ ጋር ነውና፥ ጽድቅንም አላወቅንምና። 13 በድለናል፤ ዋሽተናልም፤ አምላካችንንም መከተል ትተናል፤ ዐመፃን ተናግረናል፤ ከድተንሃልም፤ የኀጢአትንም ቃል ፀንሰን፤ ከልብ አውጥተናል። 14 ፍርድን ከመከተል ወደ ኋላ ርቀናል፤ ጽድቅም በሩቅ ቆሞአል፤ እውነትም ከመንገዳቸው ታጥቶአል፤ በቀና መንገድም መሄድ አልቻሉም። 15 ከእውነት ተወግደዋል፤ እንዳያስተውሉም ልባቸውን መልሰዋል። እግዚአብሔርም አየ፤ ፍርድም ስለሌለ ደስ አላለውም። 16 ሰውም እንደሌለ አየ፤ የሚረዳም ሰው እንደሌለ ተረዳ፤ ሰለዚህ በክንዱ ደገፋቸው፤ በይቅርታውም አጸናቸው። 17 ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፤ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቍር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ። 18 ጠላቶቹንም ያዋርዳቸው ዘንድ የበቀልና የፍዳን መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ። 19 በምዕራብ ያሉት የእግዚአብሔርን ስም፥ በፀሐይ መውጫም ያሉት ክብሩን ይፈራሉ። መቅሠፍትም ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ኀይለኛ ፈሳሽ በቍጣ ይመጣል። 20 ከጽዮን ታዳጊ ይመጣል፤ ከያዕቆብም ኀጢአትን ያርቃል። 21 “ከእነርሱ ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፤ “በአንተ ላይ ያለው መንፈሴ በአፍህም ውስጥ ያደረግሁት ቃሌ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ከአፍህ፥ ከዘርህም አፍ፥ ከዘር ዘርህም አፍ አይጠፋም፥” ይላል እግዚአብሔር። |