ኢሳይያስ 50 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እናታችሁን የፈታሁበት የፍችዋ ደብዳቤ የት አለ? ወይስ እናንተን የሸጥሁ ከአበዳሪዎች ለማን ነው? እነሆ፥ ስለ ኀጢአታችሁ ተሸጣችኋል፤ ስለ በደላችሁም እናታችሁ ተፈትታለች። 2 እነሆ፥ መጣሁ፤ ሰውም አልነበረም፤ ተጣራሁ፤ የሚመልስም አልነበረም፤ እጄ ለማዳን ጠንካራ አይደለምን? ወይስ ለማዳን አልችልምን? እነሆ፥ በገሠጽሁ ጊዜ ባሕርን አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ምድረ በዳ አደርጋቸዋለሁ፤ ውኃም በማጣት ዐሣዎቻቸው ይሞታሉ፤ በጥማትም ያልቃሉ። 3 ሰማይን በጨለማ እሸፍነዋለሁ፤ መጋረጃውንም ማቅ አደርጋለሁ።” 4 የምናገረውን ቃል አውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የጥበብ ምላስን ሰጥቶኛል፤ ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፤ ለመስማትም ጆሮን ሰጥቶኛል። 5 የጌታ የእግዚአብሔር ተግሣጽም ጆሮዬን ከፍቶአል፤ እኔም ዐመፀኛ አልነበርሁም፤ አልተከራከርሁም። 6 ጀርባዬን ለግርፋት፥ ጕንጬንም ለጽፍዐት ሰጠሁ፤ ፊቴንም ከምራቅ ኀፍረት አልመለስሁም። 7 ጌታ እግዚአብሔር ረዳኝ፤ ስለዚህም አላፈርሁም፤ ፊቴንም እንደ ባልጩት ድንጋይ አድርጌዋለሁ፤ እንዳላፍርም አውቃለሁ። 8 የሚያጸድቀኝ ቅርብ ነው፤ ከእኔስ ጋር የሚከራከር ማን ነው? እስቲ በእኔ ላይ ይነሣ፤ የሚከራከረኝስ ማን ነው? ወደ እኔ ይቅረብ። 9 እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛል፤ ማን ይጎዳኛል? እነሆ፥ ሁላችሁ እንደ ልብስ ታረጃላችሁ፤ ብልም ይበላችኋል። 10 ከእናንተ እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ማን ነው? የባሪያውንም ቃል ይስማ፤ በጨለማም የምትሄዱ፥ ብርሃንም የሌላችሁ በእግዚአብሔር ስም ታመኑ፤ በእግዚአብሔርም ተደገፉ፤ 11 እነሆ፥ እሳት የምታነድዱ፥ የእሳትንም ነበልባል ከፍ ያደረጋችሁ ሁላችሁ፥ በእሳታችሁ ብርሃንና ባነደዳችሁት ነበልባል ሂዱ፤ ስለ እኔ ይህ ይሆንባችኋል፤ በኀዘንም ትተኛላችሁ። |