ኢሳይያስ 48 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር ሁሉን የፈጠረና ሁሉን የሚያውቅ ስለ መሆኑ 1 እናንተ በእስራኤል ስም የተጠራችሁ፥ ከይሁዳም የወጣችሁ፥ በእውነት ሳይሆን፥ በጽድቅም ሳይሆን እርሱን እየጠራችሁ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም የምትምሉ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ይህን ስሙ፤ 2 በቅድስት ከተማ ስም የተጠራችሁ፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በሚባል በእስራኤል አምላክ የምትደገፉ፥ ይህን ስሙ። 3 የቀድሞውን ነገር ከጥንት ተናግሬአለሁ፤ ከአፌም ወጥቶአል፤ ድንገትም ያደረግሁት ምስክር ሆኖአል፤ እርሱም ተፈጽሞአል። 4 አንተ እልከኛ፥ አንገትህም የብረት ጅማት፥ ግንባርህም ናስ እንደ ሆነ ዐውቄአለሁ፤ 5 ስለዚህ፥ አንተ፥ “ጣዖቴ ይህን አድርጎአል፤ የተቀረጸው ምስሌና ቀልጦ የተሠራው ምስሌም ይህን አዘዙኝ” እንዳትል፥ የሚሆነውን ከመሆኑ በፊት ነገርሁህ፤ አስረዳሁህም፤ 6 ሁሉን ሰምተሃሃል፤ አላወቅህም፤ ከዛሬ ጀምሮ የሚሆነውን አዲስ ነገር ገለጥሁልህ። 7 እነርሱም አሁን እንጂ ከጥንት አልተፈጠሩም፤ አንተም፥ “እነሆ፥ ዐውቄአቸዋለሁ” እንዳትል ከዛሬ በፊት አልሰማሃቸውም። 8 አላወቅህም፤ አላስተዋልህም፤ ጆሮህን ከጥንት አልከፈትሁልህም፤ አንተ ፈጽሞ ወንጀለኛ እንደ ሆንህ፥ ከማኅፀንም ጀምረህ ተላላፊ ተብለህ እንደ ተጠራህ ዐውቄአለሁና። 9 ስለ ስሜ ቍጣዬን አሳይሃለሁ፤ እንዳላጠፋህም ግርማዬን አመጣብሃለሁ። 10 እነሆ፥ ለወጥሁህ፤ ነገር ግን በብር አይደለም፤ ከመከራም እቶን አውጥቼሃለሁ። 11 ስለ እኔ፥ ስለ ራሴ ይህን ለአንተ አደርገዋለሁ፤ ስሜ ተነቅፎአልና፤ ክብሬንም ለሌላ አልሰጥም። 12 ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ፤ እኔም ዘለዓለማዊ ነኝ። 13 እጄም ምድርን መሥርታለች፤ ቀኜም ሰማያትን አጽንታለች፤ እጠራቸዋለሁ፤ በአንድነትም መጥተው ይቆማሉ። 14 ሁሉም በአንድነት ተሰብስበው ይሰማሉ፤ ይህን ማን ነገራቸው? አንተን በመውደድ የከለዳውያንን ዘር አስወግድ ዘንድ ፈቃድህን በባቢሎን ላይ አደረግሁ። 15 እኔ ራሴ ተናግሬአለሁ፤ እኔ ጠርቼዋለሁ፤ አምጥቼዋለሁ፤ መንገዱም ትከናወንለታለች። 16 ወደ እኔ ቅረቡ፤ ይህንም ስሙ፤ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስውር አልተናገርሁም፤ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ፤ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል። 17 ታዳጊህ፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እንዲህ ይላል፥ “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ የምትሄድባትንም መንገድ እንዴት እንደምታገኝ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። 18 ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፥ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር፤ 19 ዘርህም እንደ አሸዋ የሆድህም ትውልድ እንደ ምድር ትቢያ በሆነ ነበር፤ አሁንም ስምህ ከፊቴ ባልጠፋና ባልፈረሰ ነበር። 20 ከባቢሎን ውጡ፤ ከከለዳውያንም ኰብልሉ፤ በእልልታ ድምፅ ተናገሩ፤ ይህም ይሰማ፤ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ አውሩና፥ “እግዚአብሔር ባርያውን ያዕቆብን ታድጎታል” በሉ። 21 በምድረ በዳም በተጠሙ ጊዜ፥ ውኃን ከዓለቱ ውስጥ ያፈልቅላቸው ነበር፤ ዓለቱም ተሰነጠቀ፤ ውኃውም ይፈስስላቸው ነበር፤ ሕዝቤም ይጠጡ ነበር። 22 እንግዲህ ኃጥኣን ደስታ አያደርጉም፤ ይላል እግዚአብሔር። |