ኢሳይያስ 46 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የባቢሎን አማልክት 1 ቤል ወደቀ፤ ዳጎን ተሰባበረ፤ ምስሎቻቸውም እንደ ትቢያ ሆኑ፤ አራዊትና እንስሳም ይረግጡአቸዋል፤ እንደ ፋንድያም ሸክም የሚያጸይፉ ናቸውና አያነሡአቸውም። 2 ደካሞች ናቸው፤ ኀይልም የላቸውም፤ ከጦርነትም ራሳቸውን ለማዳን አልቻሉም፤ ራሳቸው ግን ተማረኩ። 3 እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ የእስራኤልም ቤት ቅሬታ ሁሉ፥ ከማኅፀንም ጀምሮ የተሸከምኋችሁ፥ ከሕፃንነትም ጀምሮ ያስተማርኋችሁ፥ ስሙኝ። 4 እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፤ እስከ ሽበትም ድረስ እኔ ነኝ፤ እኔ እታገሣችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻለሁ፤ እኔም ይቅር እላለሁ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፤ እኔም አድናችኋለሁ። 5 እንግዲህ በማን ትመስሉኛላችሁ? የምትሳሳቱ እናንተ ሁላችሁ፥ እዩ፤ አስተውሉም። 6 ወርቁንና ብሩን ከኮሮጆ የሚያወጡና በሚዛን የሚመዝኑ እነርሱ አንጥረኛውን ይቀጥራሉ፤ እርሱም ጣዖት አድርጎ ይሠራዋል፤ ለዚያም ይጐነበሱለታል፤ ይሰግዱለትማል። 7 በጫንቃቸው ላይ ተሸክመውት ይሄዳሉ፤ በስፍራውም በአኖሩት ጊዜ በዚያ ይቆማል፤ ከስፍራውም ፈቀቅ አይልም፤ ሰውም ወደ እርሱ ቢጮህ አይሰማውም፤ ከክፉም አያድነውም። 8 ይህን ዐስቡና አልቅሱ፤ የተሳሳታችሁ ሆይ፥ ንስሓ ግቡ፤ ልባችሁንም መልሱ። 9 እኔ አምላክ ነኝና፤ ያለ እኔም ሌላ የለምና የቀድሞውንና የጥንቱን ነገር ዐስቡ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። 10 በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እናገራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች፤ የመከርሁትንም ሁሉ አደርጋለሁ እላለሁ። 11 ከምሥራቅና ከሩቅ ሀገር ስለ መከርሁት ምክር ዎፍን እጠራለሁ፤ ተናገርሁ፤ አመጣሁም፤ ፈጠርሁ፤ አደረግሁም፤ አመጣሁት፤ መንገዱንም አቀናሁለት። 12 እናንተ ከጽድቅ የራቃችሁ ልበ ጥፉዎች፥ ስሙኝ፤ 13 ጽድቄን አመጣኋት፤ ከእኔ ዘንድ የምትገኝ መድኀኒትንም አላዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኀኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ። |