ኢሳይያስ 45 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር ቂሮስን ለንጉሥነት እንደ መረጠ 1 እግዚአብሔር አምላክ ለቀባሁት፥ አሕዛብንም በፊቱ አስገዛ ዘንድ የነገሥታትንም ኀይል እጥል ዘንድ፥ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ እከፍት ዘንድ፥ ቀኝ እጁን ለያዝሁት ለቂሮስ እንዲህ ይላል፦ 2 “በፊትህ እሄዳለሁ፤ ተራሮችንም ዝቅ አደርጋለሁ፤ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ፤ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቈርጣለሁ፤ 3 በስምህም የምጠራህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ በጨለማ የነበሩትን መዛግብት እሰጥሃለሁ፤ የማይታየውንም የተደበቀውን ሀብት እገልጥልሃለሁ። 4 ስለ አገልጋዬ ስለ ያዕቆብ፥ ስለ መረጥሁትም ስለ እስራኤል ብዬ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ ተቀበልሁህም፤ አንተ ግን አላወቅኸኝም። 5 እኔ እግዚአብሔር አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ አጸናሁህ፤ አንተ ግን አላወቅኸኝም። 6 በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ እኔ እግዚአብሔር አምላክ ነኝ፤ ከእኔም ሌላ አምላክ የለም። 7 ብርሃንን ፈጠርሁ፤ ጨለማውንም ፈጠርሁ፤ ሰላምንም አደርጋለሁ፤ ክፋትንም አመጣለሁ፤ እነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። 8 “ሰማይ በላይ ደስ ይበለው፤ ደመናትም ጽድቅን ያዝንቡ፤ ምድርም መድኀኒትን ታብቅል፤ ጽድቅም በአንድነት ይብቀል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክ ፈጥሬሃለሁ። 9 “እንደ ሸክላ ሠሪ ሥራ ውብ አድርጌ ሠራሁህ፤ ምድርን የሚያርስ ሁልጊዜ ያርሳልን? ጭቃ ሠሪውን፦ ምን ትሠራለህ? እጅ የለህምና መሥራት አትችልም ይለዋልን? ጭቃ ሠሪውን ይከራከረዋልን? 10 አባቱን፦ ለምን ወለድኸኝ? እናቱንም፦ ለምን አምጠሽ ወለድሽኝ? ለሚል ወዮ! 11 “የእስራኤልም ቅዱስ የሚመጣውንም የፈጠረ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፦ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጠይቁኝ፤ ስለ እጄም ሥራ እዘዙኝ። 12 እኔ ምድርን ሠርቻለሁ፤ ሰውንም በእርስዋ ላይ ፈጥሬአለሁ፤ እኔ በእጄ ሰማያትን አጽንቼአለሁ፤ ከዋክብቶቻቸውንም ሁሉ አዝዣለሁ። 13 እኔ ቂሮስን በጽድቅ አስነሥቼዋለሁ፤ መንገዱንም ሁሉ አቀናለሁ፤ እርሱ ከተማዬን ይሠራል፤ በዋጋም ወይም በጉቦ ሳይሆን ምርኮኞችን ያወጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” 14 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ግብፅና የኢትዮጵያ ንግዶች ደከሙ፤ ቁመተ ረዥሞች የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ፤ ለአንተም ይገዙልሃል፤ እጆቻቸውን ታስረው በኋላህ ይከተሉሃል፤ በፊትህም ያልፋሉ፤ ለአንተም እየሰገዱ፦ በእውነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል። 15 አንተ እግዚአብሔር ነህ፤ የእስራኤልም መድኀኒት አምላክ እንደ ሆንህ አላወቅንህም። 16 የሚቃወሙት ሁሉም ያፍራሉ፤ ይዋረዱማል፤ አፍረውም ይሄዳሉ። 17 ደሴቶች ሆይ፥ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እግዚአብሔር ግን እስራኤልን በዘለዓለማዊ መድኀኒት ያድነዋል፤ እናንተም ለዘለዓለም አታፍሩምና አቷረዱም።” 18 ሰማይን የፈጠረ እግዚአብሔር፥ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፥ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፥ እንዲህ ይላል፥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም። 19 በስውር ወይም በጨለማ ስፍራ አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብ ዘር፦ በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም፤ ጽድቅን የምናገር፥ ቅን ነገርንም የምናገር እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 20 እናንተ ከአሕዛብ ወገን ሆናችሁ ያመለጣችሁ፥ ተሰብስባችሁ ኑ፤ በአንድነትም ተማከሩ፤ የተቀረጸውን የምስላቸውን እንጨት የሚሸከሙና ያድን ዘንድ ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ ዕውቀት የላቸውም። 21 የሚናገሩ ከሆነ ከጥንት ጀምሮ ይህን ምስክርነት ያደረገ ማን እንደ ሆነ በአንድነት ያውቁ ዘንድ ይቅረቡ። ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኀኒት ነኝ፥ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። 22 እናንተ በምድር ዳርቻ ያላችሁ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ተመለሱ፤ ትድኑማላችሁ። 23 ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፤ አትመለስምም፤ ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ምላስም ሁሉ በእግዚአብሔር ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ።” 24 ክብርና ጽድቅ ወደ እርሱ ይመጣሉ፤ ከእግዚአብሔርም የሚርቁ ሁሉ ያፍራሉ። 25 የእስራኤልም ልጆች ዘር ሁሉ በእግዚአብሔር ይጸድቃሉ፤ ይከብራሉም ይባላል። |