ኢሳይያስ 43 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዝአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ተቤዥችሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ። 2 በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ወንዞችም አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም። 3 እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኀኒትህ ነኝ፤ ግብፅንና ኢትዮጵያን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ሴዎንንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ። 4 በፊቴ የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ብዙ ሰዎችን ለአንተ ቤዛ፥ አለቆችንም ለራስህ እሰጣለሁ። 5 እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፤ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። 6 ሰሜንን፦ መልሰህ አምጣ፤ ደቡብምን፦ አትከልክል፤ ወንዶች ልጆችን ከሩቅ፥ ሴቶች ልጆችንም ከምድር ዳርቻ፥ 7 በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ” እለዋለሁ። 8 ዐይኖች እያሉአቸው የማያዩ ዕውሮችን ሕዝብ፥ ጆሮችም እያሉአቸው የማይሰሙ ደንቆሮዎችን አወጣሁ። 9 አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ አለቆችም ተከማቹ፤ ይህን ማን ይናገራል? የቀድሞውንስ ማን ይነግራችኋል? ይጸድቁ ዘንድ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፤ ሰምተውም፦ እውነትን ይናገሩ። 10 ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደ ሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ፥ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮች ሁኑ፤ እኔም ምስክር እሆናችኋለሁ ይላል እግዚአብሔር አምላክ፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልነበረም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም። 11 እኔ፥ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ የሚያድን አምላክ የለም። 12 ተናግሬአለሁ፤ አድኜማለሁ፤ መክሬማለሁ፤ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምልኮ አልነበረም፤ ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር አምላክ እንደ ሆንሁ እናንተ ራሳችሁ ምስክሮች ናችሁ፤ 13 ከጥንት ጀምሮ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፤ ወደ ኋላስ የሚመልስ ማን ነው? 14 የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፤ ስደተኞችን አስነሣለሁ፤ ከለዳውያንም በመርከብ ውስጥ ይታሰራሉ። 15 ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ እግዚአብሔር አምላክ እኔ ነኝ።” 16 በባሕር ውስጥ መንገድን በኀይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደረገ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፦ 17 እግዚአብሔር ሰረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፤ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፤ አይነሡም፤ ቀርተዋል፤ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል፤ 18 የፊተኛውን ነገር አታስታውሱ፤ የጥንቱንም ነገር አታስቡ። 19 እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፤ እናንተም አታውቁትም፤ በምድረ በዳም መንገድን፥ በበረሃም ወንዞችን አደርጋለሁ። 20 የምድረ በዳ አራዊት፥ ቀበሮችና ሰጎኖች፥ ያከብሩኛል። የመረጥሁትን ሕዝቤን አጠጣ ዘንድ በምድረ በዳ ውኃን፥ በበረሃም ወንዞችን ሰጥቻለሁና፤ 21 እነርሱም ምስጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርኋቸው ሕዝብ ናቸው፤ 22 ያዕቆብ ሆይ፥ እነሆ፥ አልጠራሁህም፤ አንተም እስራኤል ሆይ፥ አልዘበዘብሁህም፤ 23 ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎችህን አላቀረብህልኝም፤ በሌላም በሚቃጠል መሥዋዕትህ አላከበርኸኝም፤ በእህልም ቍርባን አላስቸገርሁህም፤ በዕጣንም አላደከምሁህም። 24 ዕጣንም በገንዘብ አልገዛህልኝም፤ የመሥዋዕትህንም ስብ አልተመኘሁም፤ ነገር ግን በኀጢአትህና በበደልህ በፊቴ ቁመሃል። 25 መተላለፍን፦ ስለ እኔ ስለ ራሴ ስል የምደመስስ እኔ ነኝ፤ ኀጢአትህንም አላስብም። 26 አሳስበኝ፤ በአንድነትም ሆነን እንፋረድ፤ እንድትጸድቅ አስቀድመህ በደልህን ተናገር። 27 በመጀመሪያ አባቶችህ፥ ቀጥሎም አለቆችህ በድለውኛል። 28 አለቆች መቅደሴን አረከሱ፤ ስለዚህም ያዕቆብን ለጥፋት፥ እስራኤልንም ለውርደት ሰጠሁ። |