ኢሳይያስ 42 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእግዚአብሔር ባለሟል 1 እነሆ፥ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ ያዕቆብ፤ ነፍሴ የተቀበለችው ምርጤ እስራኤልም፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያመጣል። 2 አይጮኽም፤ ቃሉንም አያነሣም፤ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። 3 የተቀጠቀጠ ሸንበቆን አይሰብርም፤ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፤ ነገር ግን በእውነት ፍርድን ያመጣል። 4 በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ያበራል እንጂ አይጠፋም፤ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ። 5 ሰማይን የፈጠረ፥ የዘረጋውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ሁሉ ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 6 “እኔ እግዚአብሔር አምላክ በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ በእጄም እይዝሃለሁ፤ አበረታሃለሁም፤ ለልጅ ልጅ ቃል ኪዳን፥ ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ። 7 የዕውራንንም ዐይን ትከፍት ዘንድ፥ የተጋዙትንም ከግዞት ቤት፥ በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ። 8 እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። 9 እነሆ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፤ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይነገር እርሱን አስታውቃችኋለሁ።” 10 ወደ ባሕር የምትወርዱ፥ በእርስዋም ውስጥ የምትጓዙ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር ዘምሩ፤ ከምድርም ዳርቻ ስሙን አክብሩ። 11 ምድረ በዳውና ከተሞችዋ፥ የቄዳርም ነዋሪዎችና መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፤ በዋሻም የሚኖሩ እልል ይበሉ፤ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። 12 ለእግዚአብሔር ክብርን ይስጡ፤ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ። 13 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይወጣል፤ ኀይለኛውንም ያጠፋል፤ ቅንአትንም ያስነሣል፤ በጠላቶቹም ላይ በኀይል ይጮኻል። 14 ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፤ እንግዲህ ለዘለዓለም ዝም እላለሁን? አሁን ምጥ እንደ ያዛት ሴት እታገሣለሁ፤ አጠፋለሁ፤ በአንድነትም እጨርሳለሁ። 15 ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፤ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፤ ኩሬዎችንም አደርቃለሁ። 16 ዕውሮችንም በማያውቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፤ የማያውቋትንም ጎዳና እንዲረግጡ አደርጋቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህንም አደርግላቸዋለሁ፤ አልተዋቸውምም። 17 በተቀረጹትም ምስሎች የሚታመኑ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች፥ “አምላኮቻችን ናችሁ” የሚሉ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ ፈጽመውም ያፍራሉ። 18 እናንተ ደንቆሮች፥ ስሙ፤ እናንተም ዕውሮች እዩ፤ ተመልከቱም። 19 ከባሪያዎች በቀር ዕውር ማን ነው? ከአለቆቻቸውስ በቀር ደንቆሮ የሆነ ማን ነው? የእግዚአብሔር ባሪያዎች ታወሩ። 20 ብዙ ነገርን ታያላችሁ፤ ነገር ግን አትጠባበቁትም፤ ጆሮዎቻችሁም ተከፍተዋል፤ ነገር ግን አትሰሙም። 21 እግዚአብሔር አምላክ ምስጋናውን ያጸድቅና ከፍ ያደርግ ዘንድ መከረ። 22 እነሆ፥ ተመለከትሁ፤ ሕዝቡ የተበዘበዘና የተዘረፈ ነው፤ ወጥመድ በሁሉም ቦታ በዋሻዎችና እነርሱን በሸሸጉባቸው ቤቶች ተጠምዶአል፤ ብዝበዛ ሆነዋል፤ የሚያድንም የለም፤ ምርኮም ሆነዋል፤ የሚያስጥላቸውም የለም። 23 ከመካከላችሁ ይህን የሚያደምጥ፥ ለሚመጣውም ጊዜ የሚሰማ ማን ነው? 24 ያዕቆብን እንዲማርኩት፥ እስራኤልንም እንዲበዘብዙት ያደረገ ማን ነው? እነርሱም የበደሉት፥ በመንገዱም ይሄዱ ዘንድ ያልወደዱት፥ ሕጉንም ያልሰሙት እግዚአብሔር እርሱ አይደለምን? 25 ስለዚህ የቍጣውን መዓትና የሰልፉን ጽናት አመጣባቸው፤ በዙሪያቸው አቃጠላቸው፤ እነርሱ ግን አላወቁም፤ በልባቸውም አላስተዋሉም። |