ኢሳይያስ 38 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሕዝቅያስ መታመምና መዳን 1 በዚያም ወራት ሕዝቅያስ ለሞት እስኪደርስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል” አለው። 2 ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፦ 3 “አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በቅን ልብ እንደ ሄድሁ፥ በፊትህም ደስ የሚያሰኝህን እንዳደረግሁ አስብ።” ሕዝቅያስም እጅግ ታላቅ ልቅሶን አለቀሰ። 4 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 5 “ሂድ፤ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፦ የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ፤ 6 አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ አድናለሁ፤ ለዚችም ከተማ እቆምላታለሁ። 7 እግዚአብሔርም የተናገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል። 8 እነሆ፥ በአባትህ የጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ ከፀሐይ ጋራ የወረደውን በደረጃዎች ያለውን ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ።” ፀሐይም በጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ የወረደበት ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ። የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ጸሎት 9 የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታምሞ ከደዌው በተፈወሰ ጊዜ የጸለየው ጸሎት ይህ ነው፦ 10 እኔ እንዲህ አልሁ፥ “በሕይወት ዘመኔ መካከል ወደ ሲኦል በሮች እገባለሁ፤ የቀረውንም ዘመኔን ተውሁ። 11 ደግሞም፦ በሕያዋን ምድር የእግዚአብሔርን ማዳን፤ የእስራኤልንም መዳን በምድር ላይ አላይም፤ ከዘመዶችም ሰውን አላይም። 12 የቀረውንም ኑሬዬን አጣሁ። ከእኔም ወጣች፥ ተለየችም። ድንኳኑን ተክሎ እንደሚያድርና እንደሚሄድ፥ ሊቈረጥ እንደ ተቃረበ ሸማም እንዲሁ ነፍሴ በላዬ ሆነች። 13 በዚያ ወራት እስኪነጋ ድረስ እንደ አንበሳ ታወክሁ፤ እንደዚሁም አጥንቶች ተቀጠቀጡብኝ፤ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ተጨነቅሁ። 14 እንደ ሸመላ እንዲሁ ጮህሁ፤ እንደ ርግብም አጕረመረምሁ፤ 15 ዐይኖች ደከሙ፤ ወደ ሰማይም ወደ እግዚአብሔር ማየት አልቻልሁም። ጌታ ሆይ፦ ይቅር በለኝ፤ የሰውነቴንም መከራ አርቅልኝ። 16 ጌታ ሆይ፥ ስለ እርስዋ እንዲህ አልሁህ፤ ነፍሴን አዳንሃት፤ ደስ አለኝ፤ በሕይወትም ኖርሁ። 17 ሰውነቴንም እንዳትጠፋ ይቅር አልሃት፤ ኀጢአቴንም ሁሉ ወደ ኋላዬ ጣልህ። 18 በመቃብር የሚኖሩ አያመሰግኑህምና፤ ሙታንም የሚያመሰግኑህ አይደሉምና፤ በሲኦልም የሚኖሩ ይቅርታህን ተስፋ አያደርጉምና። 19 እኔ ዛሬ እንደማደርግ ሕያዋን ብቻ ያመሰግኑሃል፤ ከዛሬ ጀምሮ ጽድቅህን የሚናገሩ ልጆችን እወልዳለሁ። 20 ጌታዬ ሆይ አንተ መድኀኒቴ ነህ፤ ስለዚህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት አውታር ባለው ዕቃ አንተን ማመስገንን አላቋርጥም።” 21 ኢሳይያስም ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፥ “የበለስ ጥፍጥፍ አምጥተህ በእባጩ ላይ ለብጠው፤ አንተም ትፈወሳለህ።” 22 ሕዝቅያስም፥ “ወደ እግዚአብሔር ቤት እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብሎ ነበር። |