ኢሳይያስ 37 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሕዝቅያስ የኢሳይያስን ምክር እንደ ጠየቀ 1 እንዲህም ሆነ፤ ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለበሰ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገባ። 2 የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን፥ ጸሓፊውንም ሳምናስን፥ የካህናቱንም ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ ይሄዱ ዘንድ ላካቸው። 3 እነርሱም፥ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፦ ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ፥ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል፤ ለመውለድም ኀይል የለም። 4 ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል አምላክህ እግዚአብሔር ይሰማ እንደ ሆነ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደ ሆነ፥ ስለዚህ ለቀረው ቅሬታ ጸልይ” አሉት። 5 እንዲሁ የንጉሡ የሕዝቅያስ ብላቴኖች ወደ ኢሳይያስ በመጡ ጊዜ፥ 6 ኢሳይያስ፥ “ለጌታችሁ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች ስለ ሰደቡኝ፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። 7 እነሆ፥ መንፈስን በላዩ እሰድዳለሁ፤ ወሬንም ይሰማል፤ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ በሉት” አላቸው። 8 የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ እንደ ራቀ ሰምቶ ነበርና ራፋስቂስ ተመልሶ በልብና ሲዋጋ አገኘው። 9 እርሱም፥ “የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊዋጋህ መጥቶአል” የሚል ወሬ ሰማ። በሰማም ጊዜ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፤ እንዲህ ሲል፦ 10 “ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ የምትታመንበት አምላክህ አያታልልህ። 11 እነሆ፥ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን እንዴትስ እንዳጠፉአቸው አልሰማህምን? አንተስ ትድናለህን? 12 አባቶች ያጠፉአቸውን በቴማን ያሉትን ጎዛንንና ካራንን፥ ራፌስንም የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸውን? 13 የሔማትና የአርፋድ፥ የሴፈርዋይ ከተማ፥ የሄናና የዒዋ ነገሥታት ወዴት አሉ?” 14 ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞች እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። 15 ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ጸለየ፦ 16 “አቤቱ፥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል። 17 አቤቱ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ አቤቱ፥ ዐይንህን ክፈትና በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ የላከውን የሰናክሬምን ቃል ተመልከት። 18 አቤቱ፥ በእውነት የአሦር ነገሥታት ዓለሙን ሁሉ ሀገሮቻቸውንም አፍርሰዋል፤ 19 አማልክቶቻቸውንም በእሳት አቃጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ የሰው እጅ ሥራም ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል። 20 እንግዲህ አምላካችን አቤቱ፥ የምድር ነገሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ ከእጁ አድነን።” የሰናክሬም ውድቀት 21 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስም ወደ ሕዝቅያስ ተላከ፤ እንዲህም አለው፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ የጸለይኸውን ሰምቼሃለሁ። 22 እግዚአብሔር ስለ እርሱ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ቀላል አድርጋሃለች፤ በንቀትም ሥቃብሃለች፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ራስዋን ነቅንቃብሃለች። 23 የተገዳደርኸው፥ የሰደብኸውስ ማንን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደረግህበት፥ ዐይንህንስ ወደ ላይ ያነሣህበት ማን ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ አይደለምን? 24 አንተም በመልእክተኞችህ በኩል እንዲህ ብለህ እግዚአብሔርን ተገዳደርኸው፦ በሰረገላዬ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሊባኖስ ራስ ወጥቻለሁ፤ ረዣዥሞቹንም ዝግባዎች፥ የተመረጡትንም ጥዶች እቈርጣለሁ፤ ወደ ከፍታውም ዳርቻ ወደ ዱሩ እገባለሁ፤ 25 ገድቤም ውኃውንና የውኃውን ኩሬ አደርቃለሁ። 26 “እኔ ጥንት የሠራሁትን አልሰማህምን? እኔ በቀድሞ ዘመን እንዳደረግሁት፥ አሁንም አሕዛብን በምሽጎቻቸው፥ በጽኑ ከተሞቻቸው የሚኖሩትንም ያጠፉ ዘንድ አዘዝሁ። 27 እጃቸውንም አዝላለሁ፤ ይደርቃሉም፤ በሰገነት ላይ እንዳለ ደረቅ ሣርም ሳያሸት ዋግ እንደ መታው እህልም ይሆናሉ። 28 አሁን ግን እኔ መቀመጫህንና መውጫህን፥ መግቢያህንም ዐውቄአለሁ። 29 የተቈጣኸው ቍጣና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአልና ሰለዚህ ስናጋዬን በአፍንጫህ፥ ልጓሜንም በከንፈርህ አደርጋለሁ፤ በመጣህበትም መንገድ እመልስሃለሁ። 30 “ይህም ምልክት ይሆንሃል፤ በዚህ ዓመት የዘራኸውን፥ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራላቸሁ፤ ታጭዱማላችሁ፤ ወይንንም ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ። 31 ያመለጠው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፤ ወደ ላይም ያፈራል። 32 ከኢየሩሳሌም ቅሬታ ከጽዮንም ተራራ ያመለጡት ይድናሉና፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅንአት ይህን ያደርጋል። 33 ስለዚህም እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ወደዚች ከተማ አይመጣም፤ ፍላጻንም አይወረውርባትም፤ በጋሻም አይመጣባትም፥ አያጥራትምም። 34 በመጣበትም መንገድ በዚያ ይመለሳል፤ ወደዚህም ከተማ አይመጣም ይላል እግዚአብሔር፤ 35 ስለ እኔም፥ ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ እረዳታለሁ አድናታለሁም።” 36 የእግዚአብሔርም መልአክ ወጣ፤ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰዎችን ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉም በድኖች ሆነው አገኙአቸው። 37 የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፤ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ። 38 በአምላኩም በናሳራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም ሀገር ኰበለሉ። ልጁም አስራዶን በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |