ኢሳይያስ 33 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከጠላት ስለ መዳን የተነገረ ትንቢት 1 ለሚያዋርዱአችሁ ወዮላቸው! እናንተን ግን የሚያዋርዳችሁ የለም፤ የሚወነጅላችሁ እናንተን የሚወነጅል አይደለም፤ ወንጀለኞች ይጠመዳሉ፤ ይያዛሉም፤ ብል እንደበላው ልብስም ያልቃሉ። 2 አቤቱ፥ ማረን፤ አንተን ተማምነናልና፤ የዐላውያን ዘራቸው ለጥፋት ነው፤ በመከራም ጊዜ መድኀኒታችን አንተ ነህ። 3 ከቃልህ ግርማ የተነሣ አሕዛብ ፈርተው ሸሹ፤ አሕዛብም ተበተኑ። 4 አንበጣ እንደሚሰበሰብ ትንሹም ትልቁም ምርኮአችሁ እንዲሁ ይሰበሰብላችኋል። 5 በአርያም የሚኖር ቅዱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ይኖራል፤ ጽዮንም ፍርድንና ጽድቅን ተሞላች። 6 በድኅነታችን መዝገብ በሕግ ይሰበስቡአቸዋል፤ ጥበብና ምክር፥ ጽድቅም ከእግዚአብሔር ዘንድ ናቸው፤ እነዚህም የጽድቅ መዝገቦች ናቸው። 7 እነሆ እናንተ ቀድሞ ትፈሩአቸው የነበሩ በግርማችሁ ይፈሩአችኋል፤ ከእናንተም የተነሣ ይንቀጠቀጣሉ። መልእክተኞች መራራ ልቅሶን እያለቀሱ ይላካሉ፤ ሰላምንም ይለምናሉ። 8 መንገዶች ባድማ ሆኑ፤ የአሕዛብም መፈራት ቀረ፤ ቃል ኪዳናቸውም ፈረሰ፤ እንደ ሰውም አልተመለከታቸውም። 9 ምድር አለቀሰች፤ ሊባኖስ አፈረ፤ ሳሮንም እንደ ምድረ በዳ ሆነ፤ ገሊላና ቀርሜሎስ ታወቁ። 10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “አሁን እነሣለሁ፤ አሁን እከብራለሁ፤ አሁን ከፍ ከፍ እላለሁ። 11 ዛሬ ታያላችሁ፤ ዛሬ ታደንቃላችሁ፤ የመንፈሳችሁም ኀይል ከንቱ ይሆናል፤ እሳትም ትበላችኋለች። 12 አሕዛብም በእርሻ ውስጥ ተቈርጦ እንደ ተጣለና በእሳት እንደ ተቃጠለ እሾህ የተቃጠሉ ይሆናሉ።” 13 በሩቅ ያሉ የሠራሁትን ይሰማሉ፤ በቅርብም ያሉ ኀይሌን ያውቃሉ። 14 በጽዮን ያሉ ኀጢአተኞች ፈሩ፤ መንቀጥቀጥ ዝንጉዎችን ያዘ፤ እሳት እንደሚነድድ የሚነግራችሁ ማን ነው? የዘለዓለም ሀገርንስ የሚነግራችሁ ማን ነው? 15 በጽድቅ የሚሄድ፥ ቅን ነገርንም የሚናገር፥ በደልንና ኀጢአትን የሚጠላ፥ መማለጃን ከመጨበጥ እጁን የሚያራግፍ፥ ደም ማፍሰስን ከመስማት ጆሮቹን የሚደፍን፥ ክፋትንም ከማየት ዐይኖቹን የሚጨፍን ነው። 16 እርሱ ከፍ ባለ በጽኑዕ ዓለት ዋሻ ይኖራል፤ እንጀራም ይሰጠዋል፤ ውኃውም የታመነች ትሆናለች። ስለሚመጣው የክብር ዘመን 17 ንጉሥን በክብሩ ታዩታላችሁ፤ ዐይኖቻችሁም በሩቅ ያለች ምድርን ያዩአታል። 18 ልባችሁም፥ “ጸሓፊዎች ወዴት አሉ? መማክርትስ ወዴት አሉ? የትንሹና የትልቁ ዐማፅያን ብዛትስ ወዴት አለ?” ብሎ ፍርሀትን ያስባል። 19 የማታውቋቸውን አሕዛብ አመጣባችኋለሁ፤ እናንት ዐማፅያን ሕዝብ፥ ጥልቅ ነገርን ትሰማላችሁ። የሚሰማም ማስተዋል እንደሌለው ይሆናል። 20 እነሆ፥ የመድኀኒታችንን ከተማ ጽዮንን ተመልከት፤ ዐይኖችህም ድንኳኖችዋ የማይናወጡ፥ ካስማዎችዋ ለዘለዓለም የማይነቀሉ፥ አውታሮችዋም ሁሉ የማይበጠሱ፥ የበለጸገች ከተማ ኢየሩሳሌምን ያያሉ። 21 የእግዚአብሔር ስም ለእናንተ ታላቅ ነው፤ ሀገራችሁም የሰፉ ወንዞችና ታላቅ የመስኖ ስፍራ ይሆናል፤ በዚህች መንገድ አትሄድም፤ መርከቦችም አይሄዱም። 22 አምላካችን እግዚአብሔር ታላቅ ነውና ቸል አይለንም፤ እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፤ እግዚአብሔር አምላካችን ነው። እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤ እርሱ እግዚአብሔር ያድነናል። 23 ገመዶችሽ ተበጥሰዋል፤ ጥንካሬ የላቸውምና፤ ደቀልሽ ዘመመ፤ ሸራውንም መዘርጋት አልቻለም፤ እስከሚያዝም ድረስ አላማውን አልተሸከመም። በዚያን ጊዜ የብዙ ምርኮ ተከፈለ፤ ብዙ አንካሶች እንኳ ምርኮውን ማረኩ። 24 በውስጣቸውም የሚቀመጥ ሕዝብ፦ ደክሜአለሁ አይልም፥ በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋልና። |