ኢሳይያስ 28 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ኤፍሬም የተነገረ ማስጠንቀቂያ 1 ለኤፍሬም ምንደኞች ትዕቢት አክሊል፥ ያለ ወይን ጠጅ ለሰከሩ፥ በወፍራም ተራራ ራስ ላይ ላለችም ለረገፈች ለክብር ጌጥ አበባ ወዮ! 2 እነሆ፥ ኀያል ብርቱ የሆነ የእግዚአብሔር መቅሠፍት በኀይል እንደሚወርድ የበረዶ ወጨፎ፥ እንደሚያጠፋም ዐውሎ ነፋስ፥ እንደሚያጥለቀልቅም እንደ ብዙ ውኃ ፈሳሽ በጠነከረ እጅ ወደ ምድር ይጥላል። 3 የኤፍሬም ምንደኞች ትዕቢት አክሊል በእጅና በእግር ይረገጣል፤ 4 በረዥም ተራራ ራስ ላይ ያለች የረገፈች የክብሩ ተስፋ አበባ አስቀድማ እንደምትበስል በለስ ትሆናለች፤ ሰውም ባያት ጊዜ በእጁ ሳይቀበላት ይበላት ዘንድ ይፈጥናል። 5 በዚያ ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለተረፉት ሕዝቡ የክብር የተጐነጐነ ዘውድና የተስፋ አክሊል ይሆናል። 6 ለፍርድና ከጥፋት ለሚያድናቸው ኀይል በፍርድ መንፈስ ይቀራሉ። 7 እነዚህም ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፤ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ አላዋቆች ይሆናሉ፤ ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፤ በወይን ጠጅም ይዋጣሉ፤ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይበድላሉ፤ ይህም የዐይን ምትሐት ነው፤ በፍርድ ይሰናከላሉ። 8 ማዕዱም ሁሉ ትፋትንና ርኵሰትን ተሞልቶአል፤ ንጹሕ ስፍራ እንኳን የለም። 9 ክፉን ለማን ተናገርን? ወሬን ለማን አወራን? ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን? 10 ሕማምን በሕማም ላይ፥ ተስፋንም በተስፋ ላይ ተቀበሉ፤ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው። 11 በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፤ 12 እርሱም፥ “ይህችም ለደከመ ዕረፍት ናት፤ ይህችም መቅሠፍት ናት፤” አላቸው፤ እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ። 13 ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ፥ እንዲሰበሩም፥ ተጠምደውም እንዲቸገሩ፥ የግዚአብሔርም ቃሉ በሕማም ላይ ሕማም፥ በተስፋ ላይ ተስፋ፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል። የጽዮን የማዕዘን ድንጋይ 14 ስለዚህ የተጨነቃችሁ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 15 እናንተም “ከሲኦል ጋር ተማምለናል፤ ከሞትም ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፤ ሐሰትንም መሸሸጊያን አድርገናልና፥ በሐሰትም ተሰውረናልና፥ ዐውሎ ነፋስም ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም” ትላላችሁና፥ 16 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ ዋጋው ብዙ የሆነውን፥ የተመረጠውን፥ የከበረውንና መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ አኖራለሁ፤ በእርሱም የሚያምን አያፍርም። 17 ፍርዴን ለተስፋ ይቅርታዬንም ለትክክለኛ ሚዛን አደርጋለሁ፤ በከንቱና በሐሰት የሚታመኑ ከዐውሎ ነፋስ አያመልጡም። 18 ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፤ ከኢኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይጸናም፤ የሚያልፍ ዐውሎ ነፋስ በመጣ ጊዜ ይረግጣችኋል፤ ትደክማላችሁም። 19 ባለፈም ጊዜ ይወስዳችኋል፤ ማለዳ ማለዳ በቀን ያልፋል፤ በሌሊት ክፉ ተስፋ ይሆናል፤ እናንተ ያዘናችሁ፥ መስማትን ተማሩ።” 20 መዋጋትን አንችልም፤ እናንተንም ለመሰብሰብ ደካሞች ነን። 21 እግዚአብሔርም በኃጥኣን ተራራ እንደ ነበረ ይነሣል፤ በገባዖን ሸለቆም ይኖራል፤ ሥራውን ማለት መራራ ሥራውን በቍጣ ይሠራል፤ ቍጣውም ድንቅን ያደርጋል፤ መርዙም ልዩ ነው። 22 አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚያደርገውን ያለቀና የተቈረጠ ነገርን ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራታችሁ እንዳይጸናባችሁ እናንተ ደስ አይበላችሁ። 23 አድምጡ፤ ድምፄንም ስሙ፤ ልብ አድርጉ፤ ንግግሬንም ስሙ። 24 በውኑ ገበሬ ሊዘራ ሁልጊዜ ያርሳልን? ወይስ ምድሩን ከማረሱ አስቀድሞ ዘርን ይዘራልን? ጓሉንስ ይከሰክሳልን? 25 እርሻውን ባስተካከለ ጊዜ ጥቂት ጥቍሩን አዝሙድ፥ ከሙኑንም፥ ዳግመኛም ስንዴውን፥ ገብሱንም፥ አጃውንም በየስፍራው የሚዘራ አይደለምን? 26 ምድርም የእግዚአብሔርን ፍርድ ተምራ ደስ ይላታል። 27 ጥቍሩን አዝሙድ በተሳለች ማሄጃ አያሄድም፤ የሰረገላም መንኰራኵር በከሙን ላይ አይዞርም፤ ነገር ግን ጥቍሩን አዝሙድ በሽመል፥ ከሙኑንም በበትር ይወቃል። 28 እኔ ለዘለዓለም በእናንተ ላይ አልቈጣም፤ የምሕረቴም ድምፅ አያጠፋችሁም። 29 ይህም ደግሞ ድንቅ ምክርን ከሚመክር በግብሩም ገናና ከሆነው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ወጥቶአል። እናንተ ግን ከንቱ መጽናናትን ታበዙ ዘንድ ትሻላችሁ። |