ኢሳይያስ 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ሞዓብ ጥፋት 1 ስለ ሞዓብ የተነገረ ቃል። ሞዓብ በሌሊት ትጠፋለች፤ የሞዓብም ምሽግ በሌሊት ይፈርሳል። 2 ለራሳችሁ እዘኑ፤ ጣዖታችሁና መሠዊያችሁ ያሉባት ዲቦን ትጠፋለችና፤ ወደዚያም ወጥታችሁ በሞዓብ ናባው አልቅሱ፤ ወዮም በሉ፤ ራስ ሁሉ በራ ይሆናል፤ ክንድም ሁሉ ይቈረጣል። 3 በየመንገድዋ ማቅ ታጠቁ፤ በየሰገነቶችዋም አልቅሱ፤ በየአደባባዮችዋም እንባን እጅግ እያፈሰሳችሁ ወዮ በሉ። 4 ሐሴቦንና ኤልያሊ ጮኹ፤ ድምፃቸውም እስከ ያሳ ድረስ ይሰማል፤ ስለዚህ የሞዓብ ወገብ ይታመማል። 5 ሞዓብ ራሷን ይዛ ትጮኻለች፤ ለልቧም ይረዳታል፤ እስከ ሴጎርም ድረስ ብቻዋን ታለቅሳለች። ሞዓብ እንደ ሦስት ዓመት ጥጃ ናትና በሉሒት ዐቀበት ትጮኻለች። በአሮሜዎን መንገድም ይመለሳሉ፤ ይጮኻሉም፥ ጥፋትና መናወጥም ይሆናል። 6 የኔምሬም ውኃ ይነጥፋል፤ ሣሯም ይደርቃል፤ በውስጧም ልምላሜ አይገኝም። 7 ስለዚህ ሞዓብ ይድናልን? ዐረባውያንን ወደ ሸለቆው አመጣቸዋለሁና፤ እነርሱም ይወስዷታል። 8 ጩኸት የሞዓብን ዳርቻ ሁሉ ዞረ፤ ልቅሶዋም ወደ ኤግላይምና ወደ ኢሊም ጕድጓድ ደረሰ። 9 የዲሞንም ውኃ ደም ተሞልታለች፤ በዲሞን ላይ ዐረባውያንን አመጣለሁና፤ የሞዓብንና የአርያልን ዘር፥ ከኤዶምያስም የተረፉትን ወስጄ እንደ አራዊት በምድር ላይ እሰድዳቸዋለሁ። |