ዕብራውያን 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ፍቅርና እንግዳን ስለ መቀበል 1 ከወንድሞቻችሁ ጋር በፍቅር ኑሩ። 2 እንግዳ መቀበልንም አትርሱ፤ በዚህ ምክንያት ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ለመቀበል ያታደሉ አሉና። 3 ከእነርሱ ጋር አብራችኋቸው እንደ ታሰራችሁ ሆናችሁ እስረኞችን ዐስቡ፤ መከራ የጸናባቸውንም በሥጋችሁ ከእነሱ ጋር እንዳላችሁ ሆናችሁ ዐስቡ። 4 መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው፥ ለመኝታቸውም ርኵሰት የለውም፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። 5 ገንዘብ ሳትወዱ ኑሩ፤ ያላችሁም ይበቃችኋል፤ እርሱ “አልጥልህም፤ ቸልም አልልህም” ብሎአልና። 6 አሁንም አምነን፥ “እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ አልፈራም፥ ሰው ምን ያደርገኛል?” እንበል። 7 የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው። 8 ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘለዓለም የሚኖር እርሱ ነውና። 9 ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና። 10 ድንኳኒቱን ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት ከእርሱ ሊበሉ የማይቻላቸው መሠዊያ አለን፤ 11 ሊቀ ካህናቱ የሚሠዉትን እንስሳ ደም ስለ ኀጢአት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያቀርብ ነበርና፤ ሥጋውንም ከሰፈር ውጭ ያቃጥሉት ነበር። 12 ስለዚህም ኢየሱስ ሕዝቡን በደሙ ይቀድሳቸው ዘንድ ከከተማ ውጭ ተሰቀለ። 13 አሁንም ተግዳሮቱን ተሸክመን፥ ወደ እርሱ ወደ ከተማው ውጭ እንውጣ። 14 በዚህ የሚኖር ከተማ ያለን አይደለም፤ የምትመጣውን እንሻለን እንጂ። 15 በውኑ እንግዲህ በስሙ እናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? 16 ነገር ግን ለድሆች መራራትን፥ ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና። መምህራንን ስለ ማክበር 17 ለመምህሮቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም፤ ስለ እናንተ በእግዚአብሔር ፊት ምላሽ የሚሰጡ እንደ መሆናቸው፥ ይህን ሳያዝኑ ደስ ብሎአቸው ያደርጉት ዘንድ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉና። 18 ይህም ስለ እኛ ትጸልዩ ዘንድ ይገባችኋል፤ ለሁሉ መልካም ነገርን እንደምትወዱና እንደምትሹ እናምናለን። 19 ይልቁንም ፈጥኜ እንድመለስላችሁ ይህን ታደርጉ ዘንድ አጥብቄ እለምናችኋለሁ። ቡራኬና ሰላምታ 20 በዘለዓለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው፥ 21 የሰላም አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘለዓለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። 22 ወንድሞች ሆይ፥ የምክርን ቃል እንድትቀበሉ እመክራችኋለሁ፤ በጥቂት ቃል ጽፌላችኋለሁና። 23 ወንድማችን ጢሞቴዎስ ከእኛ ወደ እናንተ እንደ ተላከ ዕወቁ፤ ፈጥኖ ከመጣ አያችኋለሁ። 24 መምህሮቻችሁን ሁሉና ቅዱሳንንም ሁሉ ሰላም በሉ፥ በኢጣልያ ያሉ ሁሉ ሰላም ብለዋችኋል። 25 የጌታችን ጸጋዉ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። ወደ ዕብራውያን የተላከው መልእክት ተፈጸመ፤ በኢጣልያ ተጻፈ፤ በጢሞቴዎስ እጅ ተላከ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን። |