ዘፀአት 39 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የልብሰ ተክህኖ አሠራር ( ዘፀ. 28፥1-14 ) 1 የቀረውም የመባ ወርቅ በእግዚአብሔር ፊት ይሠሩበት ዘንድ ንዋየ ቅድሳት ሆኖ ተሠራ። ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም ለመቅደሱ አገልግሎት ልብሶችን ሠሩ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለአሮን የተቀደሰውን ልብስ ሠሩ። 2 ልብሰ እንግድዓውንም ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይ ግምጃም፥ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም ሠሩ። 3 ወርቁንም ቀጥቅጠው እንደ ቅጠል ስስ አደረጉት፤ እንደ ፈትልም ቈረጡት። ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ ሰማያዊ፥ ሐምራዊም፥ ቀይ ግምጃም፥ የተፈተለም ጥሩ በፍታ፥ ከእርሱ ጠለፉ። 4 ሁለቱ ወገን እንዲጋጠሙ፥ በሁለት ጫንቃዎች ላይ የሚጋጠም ልብሰ መትከፍ ሠሩ። 5 እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው እርስዋን ከወርቅ፥ ከሰማያዊና ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃም፥ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም እንደ ሠሩ የልብሰ መትከፉን ቋድ ሠሩ። 6 በወርቅ ፈርጥ የተያዙ የመረግድ ድንጋዮች ሠርተው እንደ ማኅተም ቅርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም ቀረጹባቸው። 7 ለእስራኤልም ልጆች የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው፥ በልብሰ መትከፉ ጫንቃዎች ላይ አደረጓቸው። የልብሰ እንግድዓ አሠራር ( ዘፀ. 28፥15-30 ) 8 ልብሰ እንግድዓውን ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ፥ እንደ ልብሰ መትከፉ አሠራር ከወርቅና ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈትለም ከጥሩ በፍታ አደረጉ። 9 አራት ማዕዘንም ነበረ፤ ልብሰ እንግድዓውም ድርብ ነበር፤ ርዝመቱ ስንዝር፥ ወርዱም ስንዝር፥ ድርብም ነበረ። 10 ዕንቍዎቹንም በአራት ተራ አደረጉበት፤ በፊተኛውም ተራ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ መረግድ፤ 11 በሁለተኛውም ተራ በሉር፥ ሰንፔር፥ ኢያሰጲድ፤ 12 በሦስተኛውም ተራ ለግርዮን፥አካጥስ፥ አሜቴስጢኖስ፤ 13 በአራተኛውም ተራ ወርቃማ ድንጋይ፥ ቢረሌ፥ ሶም፤ ዙሪያውም በወርቅ ፈርጥ ተደረገ። 14 የዕንቍዎችም ድንጋዮች እንደ ዐሥራ ሁለቱ እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ነበሩ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ተቀረጹ፤ ስለ ዐሥራ ሁለቱም ነገዶች ነበሩ። 15 ለልብሰ እንግድዓውም የተጐነጐኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገው ከጥሩ ወርቅ ሠሩ። 16 ሁለትም የወርቅ ፈርጦች፥ ሁለትም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ ሁለቱንም የወርቅ ቀለበቶች በልብሰ እንግድዓው በሁለቱ ወገን አደረጉ። 17 ሁለቱንም የተጐነጐኑትን የወርቅ ድሪዎች በልብሰ እንግድዓው በሁለቱ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች አገቡ። 18 የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተው በልብሰ መትከፉ ጫንቃዎች ላይ ፊት ለፊት አደረጓቸው። 19 ሁለቱንም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ እነርሱንም ከልብሰ መትከፉ ፊት ለፊት ባለው በልብሰ እንግድዓው በሁለቱ ጫፎች ላይ አደረጓቸው። 20 ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ በመደረቢያው ፊት፥ ከጫንቃዎች በታች፥ በብልሃት ከተጠለፈ ከመደረቢያው ቋድ በላይ፥ በመያዣው አጠገብ አደረጓቸው። 21 ልብሰ እንግድዓው በብልሃት ከተጠለፈው ከመደረቢያው ቋድ በላይ እንዲሆን፥ ከመደረቢያው እንዳይለይ ልብሰ እንግድዓውን ከቀለበቶቹ ጋር ወደ መደረቢያው ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል አሰሩት። የልዩ ልዩ አልባሳተ ክህነት አሠራር ( ዘፀ. 28፥31-43 ) 22 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ የመደረቢያውን ቀሚስ ሞላውን በሸማኔ ሥራ ሰማያዊ አድርጎ ሠራው። 23 በቀሚሱም መካከል አንገትጌ ነበረ፤ እንዳይቀደድም በአንገትጌው ዙሪያ በአንድነት የተያያዘ ጥልፍ ነበረ። 24 በቀሚሱም ታችኛ ዘርፍ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይ ግምጃም፥ ከተፈተለ በፍታም የአበቡ ሮማኖችን አደረጉ። 25 ከጥሩ ወርቅም ሻኵራዎችን ሠሩ፤ ሻኵራዎቹንም ከሮማኖች መካከል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ አደረጉ። 26 በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ ሻኵራንና ሮማንን፥ ሻኩራንና ሮማንን እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለማገልገል አደረጉ። 27 እንደ ሸማኔ ሥራ ከጥሩ በፍታ ለአሮንና ለልጆቹ እጀ ጠባቦችን፥ ከጥሩ በፍታም አክሊልን፥ 28 ከጥሩ በፍታም መልካሞቹን ቆቦች፥ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም የእግር ሱሪዎችን፥ 29 ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊም፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይም ግምጃ በጥልፍ አሠራር የተሠራ መታጠቂያውን እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። 30 ከጥሩ ወርቅ የተለየ የወርቅ ቅጠል ሠሩ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገው፥ “ቅድስና ለእግዚአብሔር” የሚል ጻፉበት። 31 እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው፥ በአክሊሉ ላይ ያንጠለጥሉት ዘንድ ሰማያዊውን ፈትል አሰሩበት። የድንኳኑ ሥራ ፍጻሜ ( ዘፀ. 35፥10-19 ) 32 እንዲሁም የምስክሩ ድንኳን ሥራ ሁሉ ተፈጸመ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፤ እንዲሁ አደረጉ። 33 ድንኳኑንም፥ መደረቢያውንም፥ ዕቃውንም ሁሉ ወደ ሙሴ አመጡ፤ መያዣዎቹን፥ ሳንቆቹን፥ መወርወሪያዎቹን፥ ምሰሶዎቹን፥ እግሮቹንም፤ 34 ከቀይ አውራ በግ ቍርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ ከአቆስጣ ቁርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ፥ 35 የምስክሩንም ታቦት፥ መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም፤ 36 ገበታውንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ ኅብስተ ገጹንም፤ 37 ጥሩውንም መቅረዝ፥ መብራቶቹንም፥ በተራ የሚሆኑትንም ቀንዲሎች፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመብራቱንም ዘይት፤ 38 የወርቁንም መሠዊያ፥ የቅብዐቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ የድንኳኑንም ደጃፍ መጋረጃ፤ 39 የናሱንም መሠዊያ፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም፥ መቀመጫውንም፤ 40 የአደባባዩንም መጋረጆች፥ ምሰሶዎቹንም፥ እግሮቹንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቹንም፥ ካስማዎቹንም፥ ለምስክሩ ድንኳን ማገልገያ የሚሆኑትን ዕቃዎች ሁሉ፤ 41 በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነትም ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮንን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች አመጡ። 42 እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ ሁሉ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ሥራውን ሁሉ ሠሩ። 43 ሙሴም ሥራውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፥ አድርገውት ነበር፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አድርገውት ነበር፤ ሙሴም ባረካቸው። |