ዘፀአት 37 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የቃል ኪዳኑ ታቦት አሠራር ( ዘፀ. 25፥10-22 ) 1 ባስልኤልም ከማይነቅዝ ዕንጨት ታቦትን ሠራ፤ ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርድዋ አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቷም አንድ ክንድ ተኩል ነበረ። 2 በውስጥዋም፥ በውጭዋም በጥሩ ወርቅ ለበጣት፤ በዙሪያዋም የወርቅ አክሊል አደረገላት። 3 አራት የወርቅ ቀለበቶችም አደረገላት፤ እነርሱንም በአራቱ እግሮችዋ ላይ አኖረ። በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላውም ወገን ሁለት ቀለበቶች ሆኑ። 4 መሎጊያዎችዋንም ከማይነቅዝ ዕንጨት ሠራ፤ በወርቅም ለበጣቸው። 5 ታቦቷንም ለመሸከም በታቦቷ አጠገብ ባሉት አራት ቀለበቶች መሎጊያዎችዋን አገባ። 6 ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሠራላት። 7 ሁለት ኪሩቤልንም ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሠራ፤ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን አደረጋቸው። 8 ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላ ወገን በዚህና በዚያ ሁለቱን ኪሩቤል ከስርየት መክደኛው በላይ ሠራ፤ 9 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ የዘረጉ ሆኑ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ሸፈኑ፤ እርስ በርሳቸውም ተያዩ፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ መክደኛው ተመለከቱ። የኅብስተ ገጹ ገበታ አሠራር ( ዘፀ. 25፥23-30 ) 10 ርዝመቱ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነውን ገበታ ከማይነቅዝ ዕንጨት ሠራ። 11 በጥሩም ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት። 12 በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አደረገለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አደረገለት። 13 አራትም የወርቅ ቀለበቶች አደረገለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አደረገ። 14 ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶች በክፈፉ አቅራቢያ ነበሩ። 15 ገበታውንም ይሸከሙባቸው ዘንድ መሎጊያዎቹን ከማይነቅዝ ዕንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። 16 ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ በገበታው ላይ የሚኖሩትን ዕቃዎች፥ ወጭቶቹንና ጭልፋዎቹን፥ ጽዋዎቹንም፥ መቅጃዎቹንም ከጥሩ ወርቅ አደረጋቸው። የመቅረዙ አሠራር ( ዘፀ. 25፥31-40 ) 17 መቅረዝዋንም ከጥሩ ወርቅ አደረገ፤ መቅረዝዋንም ከእግርዋና ከአገዳዋ ጋር በተቀረጸ ሥራ አደረገ፤ ጽዋዎችዋን፥ ጕብጕቦችዋን፥ አበቦችዋን ከዚያው በአንድነት አደረገ። 18 በስተጎንዋ ስድስት ቅርንጫፎች ወጡላት፤ ሦስቱ የመቅረዝዋ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስቱም የመቅረዝዋ ቅርንጫፎች በሁለተኛው ወገን ወጡ። 19 በአንደኛው ቅርንጫፍ ጕብጕቡንና አበባውን፥ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕቡንና አበባውን፥ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ እንዲሁም ከመቅረዝዋ ለወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አደረገ። 20 በመቅረዝዋም ጕብጕቦችዋንና አበቦችዋን፥ አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አደረገ። 21 ከመቅረዝዋ ለወጡ ለስድስት ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ከሁለትም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ ነበረ። 22 ጕብጕቦችዋና ቅርንጫፎችዋ ከእርሱ ጋር አንድ ነበሩ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ተሠርቶ ነበር። 23 ሰባቱንም መብራቶችዋን መኰስተሪያዎችዋንም፥ የኵስታሪ ማድረጊያዎችዋንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። 24 መቅረዙንም፥ ዕቃውንም ሁሉ ከአንድ መክሊት ጥሩ ወርቅ አደረገ። የዕጣን መሠዊያው አሠራር ( ዘፀ. 30፥1-5 ) 25 የዕጣን መሠዊያንም ከማይነቅዝ ዕንጨት ሠራ፤ ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱ አንድ ክንድ፤ አራት ማዕዘን ነበር፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ነበር፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድነት የተሠሩ ነበሩ። 26 ላይኛውንና የግድግዳውንም ዙሪያ፥ ቀንዶቹንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገበት። 27 ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አደረገበት፤ በዚህና በዚያ በሁለቱም ጎን አደረጋቸው፤ ለመሸከምም የመሎጊያዎች መግቢያ ነበሩ። 28 መሎጊያዎቹንም ከማይነቅዝ ዕንጨት አደረገ፤ በወርቅም ለበጣቸው። 29 የተቀደሰውንም የቅብዐቱን ዘይት፥ ጥሩውንም የጣፋጭ ሽቱ ዕጣን በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ አደረገ። |