ዘፀአት 33 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እስራኤል ከሲና ተራራ እንደ ተነሡ 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ “ሂድ፤ አንተ ከግብፅ ከአወጣኸው ሕዝብህ ጋር ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ለዘራችሁ እሰጣታለሁ ብዬ ወደ ማልሁባት ምድር ውጣ። 2 መልአኬንም ከአንተ ጋር በፊትህ እልካለሁ፤ ከነዓናዊውን፥ አሞሬዎናዊውንም፥ ኬጤዎናዊውንም፥ ፌርዜዎናዊውንም፥ ጌርጌሴዎናዊውን፥ ኤዌዎናውዊውንም፥ ኢያቡሴዎናዊውንም ያወጣቸዋል። 3 ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው ምድር አስገባሃለሁ፤ አንገተ ደንዳና ስለሆኑ ሕዝብህ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ እኔ ከአንተ ጋር አልወጣም።” 4 ሕዝቡም ይህን ክፉ ወሬ ሰምተው ታላቅ ኀዘን አዘኑ፤ 5 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “ለእስራኤል ልጆች እናንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፤ ሌላ መቅሠፍት እንዳላመጣባችሁና እንዳላጠፋችሁ ተጠንቀቁ፤ አሁንም የክብር ልብሳችሁንና ጌጣችሁን ከእናንተ አውጡ፤ የማደርግባችሁንም አሳያችኋለሁ በላቸው” አለው። 6 የእስራኤልም ልጆች ከኮሬብ ተራራ ጀምረው ልብሶቻቸውንና ጌጦቻቸውን አወጡ። ደብተራ ኦሪት 7 ሙሴም ድንኳኑን ወስዶ ከሰፈር ውጭ ይተክለው ነበር፤ ከሰፈሩም ራቅ ያደርገው ነበር፤ “የምስክሩም ድንኳን” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርንም የፈለገ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ወደአለው ወደ ድንኳኑ ይወጣ ነበር። 8 ሙሴም ከሰፈር ውጭ ወደአለው ድንኳን በሄደ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ፥ እያንዳንዱም በድንኳኑ ደጃፍ እየጠበቀ ይቆም ነበር፤ ሙሴም ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ይመለከቱት ነበር። 9 ሙሴም ወደ ድንኳኑ በገባ ጊዜ ዐምደ ደመና ይወርድ ነበር፤ በድንኳኑም ደጃፍ ይቆም ነበር፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ይናገረው ነበር። 10 ሕዝቡም ሁሉ ዐምደ ደመናው በድንኳኑ ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ተነሥቶ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ይሰግድ ነበር። 11 እግዚአብሔርም፥ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር። ሙሴም ወደ ሰፈሩ ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን አገልጋዩ ብላቴና የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይወጣም ነበር። ሙሴና የእግዚአብሔር ክብር 12 ሙሴም እግዚአብሔርን፥ “እነሆ፥ አንተ፦ ይህን ሕዝብ አውጣ ትለኛለህ፤ ነገር ግን ከእኔ ጋር የምትልከውን አላስታወቅኸኝም። አንተም ከሁሉ ይልቅ ዐወቅሁህ፥ ደግሞም በእኔ ፊት ሞገስን አገኘህ አልኸኝ። 13 አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ዐውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ ይህም ትልቅ ሕዝብ ሕዝብህ እንደ ሆነ ዐውቅ ዘንድ ተገለጥልኝ” አለው። 14 እግዚአብሔርም፥ “እኔ በፊትህ እሄዳለሁ፥ አሳርፍህማለሁ” አለው። 15 እርሱም፥ “አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን። 16 በምድርም ከአለው ሕዝብ ሁሉ እኔና ሕዝብህ ተለይተን እንከብር ዘንድ አንተ ከእኛ ጋር ካልሄድህ፥ እኔና ሕዝብህ በአንተ ዘንድ በእውነት ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል?” አለው። 17 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ይህን ያልኸኝን ነገር አደርግልሃለሁ፤ በፊቴ ሞገስን አግኝተሀልና ከሁሉ ይልቅ ዐውቄሃለሁና”አለው። 18 እርሱም፥ “ክብርህን አሳየኝ” አለው። 19 እግዚአብሔርም፥ “እኔ በክብሬ በፊትህ አልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ እጠራለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፤ የምምረውንም እምራለሁ” አለ። 20 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም” አለ። 21 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “እነሆ፥ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዐለቱም ላይ ትቆማለህ፤ 22 ክብሬም በአለፈ ጊዜ በአለቱ ስንጥቅ ውስጥ አኖርሃለሁ፤ 23 እስከ አልፍም ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፤ በዚያ ጊዜ ጀርባዬን ታያለህ፤ ፊቴ ግን ለአንተ አይታይም።” |