ዘፀአት 29 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለአሮንና ለልጆቹ ክህነትን ለመስጠት የተሰጠ ሕግ ( ዘሌ. 8፥1-36 ) 1 “እኔንም በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀድሳቸው ዘንድ የምታደርግላቸው ነገር ይህ ነው፤ ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ትወስዳለህ። 2 ቂጣ እንጀራ፥ በዘይትም የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ ከመልካም ስንዴ ታደርጋለህ። 3 በአንድ መሶብም ታደርጋቸዋለህ፤ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋር በመሶብ ታቀርባቸዋለህ። 4 አሮንንና ልጆቹን ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ታቀርባቸዋለህ፤ በውኃም ታጥባቸዋለህ። 5 ልብሶችን ወስደህ ለወንድምህ ለአሮን የነጭ ሐር እጀ ጠባብ ቀሚስ፥ ልብሰ መትከፍና ልብሰ እንግድዓ ታለብሰዋለህ፤ ለእርሱም ልብሰ እንግድዓውን ከልብሰ መትከፉ ጋር አያይዝለት። 6 አክሊልንም በራሱ ላይ ታደርጋለህ፤ የወርቁንም ቀጸላ በአክሊሉ ላይ ታኖራለህ። 7 የቅብዐትንም ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ ታፈስሰዋለህ፤ ትቀባውማለህ። 8 ልጆቹንም ታቀርባቸዋለህ፤ ቀሚሶችንም ታለብሳቸዋለህ፤ 9 በመታጠቂያም ታስታጥቃቸዋለህ፤ ቆብንም ታደርግላቸዋለህ፤ ለዘለዓለም ሥርዐትም ክህነት ይሆንላቸዋል፤ እንዲሁም የአሮንንና የልጆቹን እጆች ትቀባቸዋለህ። 10 “ወይፈኑንም ወደ ምስክሩ ድንኳን በር ታቀርበዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም በምስክሩ ድንኳን በር በእግዚአብሔር ፊት እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናሉ። 11 ወይፈኑንም በምስክሩ ድንኳን በር አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ታርደዋለህ። 12 ከወይፈኑም ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣትህ ትረጨዋለህ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ታፈስሰዋለህ። 13 የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ሁሉ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በላያቸውም ያለውን ስብ ወስደህ በመሠዊያው ላይ ታስቀምጣለህ። 14 የወይፈኑን ሥጋ ግን፥ ቍርበቱንም፥ ፈርሱንም ከሰፈር ውጭ በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የኀጢአት መሥዋዕት ነውና። 15 “አንደኛውንም አውራ በግ ትወስደዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ። 16 አውራውንም በግ ታርደዋለህ፤ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ትረጨዋለህ። 17 አውራውንም በግ በየብልቱ ትቈርጠዋለህ፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ ታጥባለህ፤ ከብልቱና ከራሱም ጋር ታኖረዋለህ። 18 አውራንም በግ በሞላው በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ፤ ስለ ጣፋጭ ሽታ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው፤ ለእግዚአብሔር የቀረበ የእሳት ቍርባን ነው። 19 “ሁለተኛውንም አውራ በግ ትወስደዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በአውራው በግ ራስ ላይ ይጭናሉ። 20 አውራውንም በግ ታርደዋለህ፤ ደሙንም ትወስዳለህ፤ የአሮንንም የቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የቀኝ እጁንና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ጫፍ፥ የልጆቹንም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ታስነካለህ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ትረጨዋለህ። 21 በመሠዊያውም ላይ ካለው ደም ከቅብዐት ዘይትም ወስደህ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ ከእርሱም ጋር ባሉት በልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ ትረጨዋለህ፤ እርሱም ልብሶቹም፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹ፥ ልብሶቻቸውም ይቀደሳሉ። 22 የበጉንም ስብ፥ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በላያቸውም ላይ ያለውን ስብ፥ የቀኙንም ወርች ትወስዳለህ፤ የሚቀደሱበት ነውና። 23 በእግዚአብሔር ፊት በመሶብ ካለው አንድ የዘይት እንጀራና አንድ የቂጣ እንጐቻ ትወስዳለህ፤ 24 ሁሉንም በአሮን እጆችና በልጆቹ እጆች ታኖረዋለህ፤ ለሚለይ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ትለየዋለህ። 25 ከእጃቸውም ትቀበለዋለህ፤ በመሥዊያውም ላይ ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በእግዚአብሔር ፊት በጎ መዓዛ እንዲሆን ታቃጥለዋለህ፤ እርሱ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ነው። 26 “ለአሮንም ክህነት የታረደውን የአውራውን በግ ፍርምባ ወስደህ ለሚለይ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ትለየዋለህ፤ እርሱም የአንተ ወግ ይሆናል። 27 ከሚካኑበትም አውራ በግ የተወሰደ ለአሮንና ለልጆቹ ወግ የሚሆን ለመሥዋዕት የተለየውን ፍርምባና የተነሣውን ወርች ትቀድሳለህ። 28 ይህም የተለየ ቍርባን ነውና ከእስራኤልልጆች ዘንድ ለዘለዓለም የአሮንና የልጆቹ ሕግ ይሁን፤ የእስራኤል ልጆች የሚያቀርቡት የደኅንነት መሥዋዕታቸው የተለየ ቍርባን ይሆናል፤ ለእግዚአብሔር የተለየ ቍርባን ይሆናል። 29 “የአሮንም የቅድስናው ልብስ ይቀቡበትና እጆቻቸው ይቀደሱበት ዘንድ ከእርሱ በኋላ ለልጆቹ ይሁን። 30 ከልጆቹም በእርሱ ፋንታ ካህን የሚሆነው በመቅደስ ለማገልገል ወደ ምስክሩ ድንኳን ሲገባ ሰባት ቀን ይልበሰው። 31 “የቅድስናውንም በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ትቀቅለዋለህ። 32 አሮንና ልጆቹም የአውራውን በግ ሥጋ፥ በመሶብም ያለውን እንጀራ በምስክሩ ድንኳን በር ይበሉታል። 33 ለመክበራቸው እጆቻቸውን ይቀድሱ ዘንድ በተቀደሱበት በዚያ ቦታ ይብሉት፤ የባዕድ ልጅ ግን አይብላው፤ የተቀደሰ ነውና። 34 ከቅድስናው መሥዋዕት ሥጋ ወይም እንጀራ እስከ ነገ ቢተርፍ፥ የቀረውን በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የተቀደሰ ነውና አይበላም። 35 “እንዳዘዝሁህም ሁሉ ለአሮንና ለልጆቹ እንዲህ አድርግ፤ ሰባት ቀን እጆቻቸውን ትቀድሳለህ። 36 ዕለት ዕለትም ስለ ማስተስረይ ለኀጢአት መሥዋዕት ወይፈኑን ታቀርባለህ፤ ማስተስረያም ባደረግህ ጊዜ መሠዊያውን ታነጻዋለህ፤ ቅዱስም ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ። 37 ሰባት ቀን መሠዊያውን ታነጻዋለህ፤ ትቀድሰውማለህ፤ መሠዊያውም ቅዱሰ ቅዱሳን ይሆናል፤ መሠዊያውንም የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። የዘወትር መሥዋዕት ( ዘኍ. 28፥1-8 ) 38 “በመሠዊያውም ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ በቀን በቀን ዘወትር በመሠዊያው ላይ ሁለት ንጹሓን የዓመት ጠቦቶች ታቀርባለህ። 39 አንዱን ጠቦት በነግህ፥ ሁለተኛውንም ጠቦት በሠርክ መሥዋዕት አድርገህ ታቀርበዋለህ። 40 ከአንዱ ጠቦትም ጋር የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ ዐሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት፥ ደግሞ ለመጠጥ ቍርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ታቀርባለህ። 41 ሁለተኛውንም ጠቦት በሠርክ ታቀርበዋለህ፤ እንደ ነግሁም የእህልና የመጠጥ ቍርባን ታደርግበታለህ፤ ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን የእሳት ቍርባን ይሆናል። 42 በዚያ እናገርህ ዘንድ ለአንተ በምገለጥበት በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ለልጅ ልጃችሁ የዘወትር መሥዋዕት ይሆናል። 43 በዚያም የእስራኤልን ልጆች አዝዛለሁ፤ በክብሬም እቀደሳለሁ። 44 የምስክሩንም ድንኳን መሠዊያውንም እቀድሳለሁ፤ በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን እቀድሳለሁ። 45 በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፤ አምላካቸውም እሆናቸዋለሁ። 46 በእነርሱ እጠራ ዘንድ፥ አምላክም እሆናቸው ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው አምላካቸው እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። |