ዘፀአት 28 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ልብሰ ተክህኖ አሠራር ( ዘፀ. 39፥1-7 ) 1 “አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፤ አሮንን የአሮንንም ልጆች፥ ናዳብን፥ አብዩድንም፥ አልዓዛርንም ኢታምርንም አቅርብ። 2 የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለመለያ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን ሥራለት። 3 አንተም የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው፥ በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር። እነርሱም ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ ለአሮን ለቤተ መቅደስ የሚሆን የተለየ ልብስ ይሥሩ፤ 4 የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ ልብሰ እንግድዓ፥ ልብሰ መትከፍ፥ ቀሚስም፥ ዥንጕርጕር እጀ ጠባብ፥ መጠምጠሚያ፥ መታጠቂያም፤ እነዚህንም በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን፥ ለልጆቹም የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ። 5 ወርቅ፥ ሰማያዊና ሐምራዊ፥ ቀይ ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም ይውሰዱ። 6 “ልብሰ መትከፉንም ከወርቅ፥ ከሰማያዊና ከሐምራዊ፥ ከተፈተለ ከቀይ ግምጃ በግብረ መርፌ የተሠራ፥ የተለየ የሽመና ሥራ ያድርጉ። 7 ሁለቱ ወገን አንድ እንዲሆን በሁለቱ ጫንቃ ላይ የሚጋጠም ጨርቅ ይሁን። 8 በላዩም የተጠለፈው የልብሰ መትከፍ ቋድ እንደ እርሱ፥ ከእርሱም ጋር አንድ ይሁን፤ ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለ፥ ከጥሩ በፍታም የተሠራ ይሁን። 9 ሁለትም የመረግድ ድንጋይ ወስደህ የእስራኤልን ልጆች ስም ስማቸውን ቅረጽባቸው፤ 10 እንደ አወላለዳቸው ስድስት ስሞችን በአንዱ ድንጋይ፥ የቀሩትንም ስድስቱን ስሞች በሌላው ድንጋይ ቅረጽ። 11 በቅርጽ ሠራተኛ ሥራ እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በሁለት ድንጋዮች ቅረጽ፤ በወርቅም ፈርጥ አድርግ። 12 ለእስራኤል ልጆችም የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ ሁለቱን ዕንቍዎች በልብሰ መትከፉ ጫንቃዎች ላይ ታደርጋለህ፤ አሮንም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ ለመታሰቢያ ስማቸውን በእግዚአብሔር ፊት ይሸከማል። 13 ፈርጦችንም ከጥሩ ወርቅ ሥራ፤ 14 ሁለት ቋዶችንም ከጥሩ ወርቅ እንደ ተጐነጐነ ገመድ አድርገህ ሥራ፤ የተጐነጐኑትንም ቋዶች በፈርጦቹ ላይ አንጠልጥል። ልብሰ እንግድዓ ( ዘፀ. 39፥8-21 ) 15 “ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ የፍርዱን ልብሰ እንግድዓ ሥራው፤ እንደ ልብሰ መትከፍም አሠራር ሥራው፤ ከወርቅና ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይም ግምጃ፥ ከጥሩ በፍታም ሥራው። 16 ርዝመቱ ስንዝር ስፋቱም ስንዝር፥ ሆኖ አራት ማዕዘን ድርብ ይሁን። 17 በአራት ተራ የሆነ የዕንቍ ፈርጥ አድርግበት፤ የድንጋዮቹም ተራ ሰርድዮን፥ ጳዝዮን፥ መረግድ ነው፤ ይህም መጀመሪያው ተራ ነው፤ 18 ሁለተኛውም ተራ በሉር፥ ሰንፔር፥ ኢያሰጲድ፤ 19 ሦስተኛውም ተራ ለግርዮን፥ አካጥስ፥ አሜቴስጢኖስ፤ 20 አራተኛውም ተራ ወርቃማ ድንጋይ፥ ቢረሌ፥ ሶም በየተራቸው በወርቅ የተለበጡና የታሠሩ ይሆናሉ። 21 የዕንቍም ድንጋዮች እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ዐሥራ ሁለት ይሆናሉ፤ በየስማቸውም ማኅተም አቀራረጽ ይቀረጹ፤ ስለ ዐሥራ ሁለቱ ነገዶችም ይሁኑ። 22 ለልብሰ እንግድዓውም የተጐነጐኑትን ቋዶች እንደ ገመድ አድርገህ ከጥሩ ወርቅ ሥራቸው። 23 ለልብሰ እንግድዓውም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፤ ሁለቱንም ቀለበቶች በልብሰ እንግድዓው በሁለቱ ወገን አድርጋቸው። 24 የተጐነጐኑትንም ሁለቱን የወርቅ ቋዶች በልብሰ እንግድዓው በሁለት ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለት ቀለበቶች ታገባቸዋለህ። 25 የሁለቱንም ቋዶች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተህ በልብሰ መትከፉ ጫንቃዎች ላይ በስተፊት በመጋጠሚያቸው ታደርጋቸዋለህ። 26 ሁለት የወርቅ ቀለበቶችንም ሥራ፤ እነርሱንም ልብሰ መትከፉ በውስጥ በሚያልፍበት በከንፈሩ በኩል በሁለቱ የልብሰ እንግድዓ ጫፎች ላይ ታኖራቸዋለህ። 27 ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፤ በልብሰ መትከፉ ፊት ከጫንቃዎች በታች በብልሃት ከተጠለፈ ከልብሰ መትከፉ ቋድ በላይ በመጋጠሚያው አጠገብ ታደርጋቸዋለህ። 28 ልብሰ እንግድዓውም በብልሃት ከተጠለፈ ከልብሰ መትክፉ ቋድ በላይ እንዲሆን፥ ከልብሰ መትከፉም እንዳይለይ፥ ልብሰ እንግድዓውን ከቀለበቶቹ ወደ ልብሰ መትከፉ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል ያያይዙታል። 29 አሮንም ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ለዘለዓለም መታሰቢያ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርዱ ልብሰ እንግድዓ ውስጥ በልቡ ላይ ይሸከም። 30 በፍርዱ ልብሰ እንግድዓም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን ታደርጋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ወደ ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆናሉ፤ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ የእስራኤልን ልጆች ፍርድ በልቡ ላይ ይሸከማል። ልዩ ልዩ አልባሰ ክህነት ( ዘፀ. 39፥22-31 ) 31 “ቀሚሱንም ሁሉ ሰማያዊ አድርገው። 32 ከላይም በመካከል አንገትጌ ይሁንበት፤ እንዳይቀደድም በግብረ መርፌ የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ይሁንበት። 33 በታችኛውም ዘርፍ ዙሪያ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይም ግምጃ ሮማኖችን አድርግ፤ በእነዚያም መካከል በዙሪያው በተመሳሳይ ቅርጽ የወርቅ ሮማኖች ሻኵራዎችን አድርግ፤ 34 የወርቅ ሻኩራ ሮማንም፥ ሌላም የወርቅ ሻኩራ ሮማንም በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያውን ይሆናሉ። 35 በማገልገል ጊዜም በአሮን ላይ ይሆናል፤ እርሱም እንዳይሞት ወደ መቅደሱ በእግዚአብሔር ፊት ሲገባና ሲወጣ ድምፁ ይሰማል። 36 “ከጥሩ ወርቅም የወርቅ ቅጠል ሥራ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ፦ ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ትቀርጽበታለህ። 37 በሰማያዊም ፈትል በመጠምጠሚያው ላይ በስተፊቱ ታንጠለጥለዋለህ ። 38 በአሮንም ግንባር ላይ ይሆናል፤ አሮንም የእስራኤል ልጆች በሚያቀርቡትና በሚቀድሱት በቅዱሱ ስጦታቸው ሁሉ ላይ የሠሩትን ኀጢአት ይሸከም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀባይነት ያለው እንዲሆንላቸው ሁልጊዜ በግንባሩ ላይ ይሁን። 39 ቀሚሱንም ከጥሩ በፍታ ዝንጕርጕር አድርገህ፥ አክሊልን ከበፍታ ትሠራለህ፤ በጥልፍ አሠራርም መታጠቂያ ትሠራለህ። 40 ለአሮንም ልጆች የበፍታ ቀሚሶችን፥ መታጠቂያዎችንም፥ ቆቦችንም ለክብርና ለመለያ ታደርግላቸዋለህ። 41 ይህንም ሁሉ ወንድምህን አሮንን፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹን ታለብሳቸዋለህ፤ በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀባቸዋለህ፤ እጆቻቸውንም ታነጻለህ፤ ትቀድሳቸውማለህ። 42 ኀፍረተ ሥጋቸውንም ይከድኑበት ዘንድ የተልባ እግር ሱሪ ታደርግላቸዋለህ፤ ከወገባቸውም እስከ ጭናቸው ይደርሳል፤ 43 እንዲሁም ኀጢአት እንዳይሆንባቸው፥ እንዳይሞቱም፥ ወደ ምስክሩ ድንኳን ሲገቡ፥ በመቅደሱም ያገለግሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ በአሮንና በልጆቹ ላይ ይሆናል፤ ለእርሱ፥ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም ሥርዐት ይሆናል። |