ዘዳግም 20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ጦርነት የተሰጡ መመሪያዎች 1 “ጠላቶችህን ለመውጋት በወጣህ ጊዜ፥ ፈረሶችንና ፈረሰኞችን ሕዝቡንም ከአንተ ይልቅ በዝተው ባየህ ጊዜ፥ ከግብፅ ሀገር ያወጣህ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና አትፍራቸው። 2 ወደ ጦርነትም በቀረባችሁ ጊዜ ካህኑ ይቅረብ፤ ለሕዝቡም እንዲህ ብሎ ይንገራቸው፦ 3 እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ዛሬ ጠላቶቻችሁን ለመውጋት ትሄዳላችሁ፤ ልባችሁ አይታወክ፤ አትፍሩ፤ አትሸበሩ፤ ከፊታቸውም ፈቀቅ አትበሉ፤ 4 ከእናንተ ጋር የሚሄድ፥ ያድናችሁም ዘንድ ጠላቶቻችሁን ስለ እናንተ የሚወጋ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነውና። 5 ጸሐፍትም ለሕዝቡ እንዲህ ብለው ይናገሩ፦ አዲስ ቤት ሠርቶ ያላስመረቀ ሰው ቢኖር በጦርነት እንዳይሞት ሌላም ሰው እንዳያስመርቀው ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ። 6 ወይንም ተክሎ ደስ ያልተሰኘበት ሰው ቢኖር በጦርነት እንዳይሞት ሌላም ሰው ደስ እንዳይሰኝበት ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ። 7 ሚስትም አጭቶ ያላገባት ሰው ቢኖር በጦርነት እንዳይሞት ሌላም ሰው እንዳያገባት ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ። 8 ጸሐፍቱም ደግሞ ጨምረው፦ ማንም ፈሪና ልበ ድንጉጥ ሰው ቢሆን የወንድሞቹን ልብ እንደ እርሱ እንዳያስፈራ ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ ብለው ለሕዝቡ ይናገሩ። 9 ጸሐፍቱም ለሕዝቡ ነግረው በጨረሱ ጊዜ ከታላላቁ ሕዝብ መካከል የሠራዊት አለቆችን ይሹሙ። 10 “ለመዋጋት ወደ አንዲት ከተማ በደረስህ ጊዜ አስቀድመህ በሰላም ቃል ጥራቸው። 11 የሰላም ቃልም ቢመልሱልህ ደጅም ቢከፍቱልህ፥ በከተማው ያለው ሕዝብ ሁሉ ይገብሩልህ፤ አገልጋዮችም ይሁኑህ። 12 የሰላም ቃልም ባይመልሱልህ ከአንተም ጋር መዋጋት ቢወድዱ፥ አንተ ከተማዪቱን ትከብባለህ፤ 13 አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ በሰጣት ጊዜ፥ በእርስዋ ያሉትን ወንዶች ሁሉ በሰይፍ ስለት ትገድላቸዋለህ፤ 14 ከሴቶቹና ከጓዙ በቀር እንስሶቹን፥ በከተማዪቱም ያለውን ምርኮ ሁሉ ዘርፈህ ለአንተ ትወስዳለህ፤ አምላክህም እግዚአብሔር የሚሰጥህን የጠላቶችህን ምርኮ ትበላለህ። 15 አምላክህ እግዚአብሔር ትወርስ ዘንድ ምድራቸውን ከሚሰጥህ ከእነዚህ አሕዛብ ከተሞች ባይደሉት ከአንተ እጅግ በራቁት ከተሞች ሁሉ እንዲሁ ታደርጋለህ። 16 ከእነርሱም ምንም ነፍስ አታድንም። 17 ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር እንዳዘዘህ ኬጤዎናዊዉን፥ አሞሬዎናዊዉን፥ ከነዓናዊዉንም፥ ፌርዜዎናዊዉንም፥ ኤዌዎናዊዉንም፥ ኢያቡሴዎናዊዉንም፥ ጌርጌሴዎናዊዉንም ፈጽመህ ትረግማቸዋለህ። 18 ለአማልክቶቻቸው ያደረጉትን ርኵሰት ሁሉ ታደርጉ ዘንድ እንዳያስተምሩአችሁ፥ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት እንዳትሠሩ ትረግማቸዋለህ። 19 “ከተማዪቱን ለመውጋትና ለመውሰድ ብዙ ቀን ብትከብባት፥ ምሳርህን አንሥተህ ዛፎችዋን አትቍረጥ፤ ከእነርሱ ትበላለህና አትቍረጣቸው፤ ወደ አንተ ይመጣና ወደ ቅጥርህም ይገባ ዘንድ የምድር ዛፍ ሰው መሆኑ ነውን? 20 ለመብል የማይሆኑትን የምታውቃቸውን ዛፎች ታጠፋቸዋለህ፤ ትቈርጣቸውማለህ፤ እስክታሸንፋትም ድረስ በምትዋጋህ ከተማ ላይ ምሽግ ትመሽጋለህ። |