2 ዜና መዋዕል 36 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢዮአክስ ዘመነ መንግሥት ( 2ነገ. 23፥30-35 ) 1 የሀገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወስደው በአባቱ ፋንታ በኢየሩሳሌም አነገሡት። 2 ኢዮአክስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ሦስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ። 2 ‘ሀ’ የእናቱም ስም ከሎቤና የኤርምያስ ልጅ አሚጣል ነበረች። 2 ‘ለ’ አባቶቹ እንደ ሠሩት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራን ሠራ። በኢየሩሳሌምም እንዳይነግሥ በኤማት ምድር በዴብላታ ፈርዖን ኒካዑ ማርኮ አሰረው። 3 ንጉሡም ወደ ግብፅ ወሰደው፤ በሀገሩም ላይ መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ግብር ጣለበት። 4 የግብፅም ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ የይሁዳን ንጉሥ የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ ፋንታ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ፤ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠ፤ ፈርዖን ኒካዑም ወንድሙን ኢዮአክስን ይዞ ወደ ግብፅ ወሰደው። በዚያም ሞተ። 4 ‘ሀ’ ወርቅንና ብርን ለፈርዖን ሰጠ። በዚያን ጊዜም ምድር በፈርዖን ትእዛዝ ብር መገበሯን ጀመረች። 4 ‘ለ’ እያንዳንዱም እንደሚችለው ለፈርዖን ኒካዑ እንዲገብር ከሀገሪቱ ሕዝብ ወርቅንና ብርን ጠየቀ። 5 ኢዮአቄምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ዘካራ የምትባል የኔሬያሳ ልጅ የራማ ሴት ነበረች፤ አባቶቹም እንዳደረጉ በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 5 ‘ሀ’ በእነዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደዚያ ሀገር መጣና ሦስት ዓመት ተገዛለት። ከእርሱም ከዳ። 5 ‘ለ’ እግዚአብሔርም የከለዳውያንንና የሶርያውያንን፥ የሞዓባውያንንና የአሞናውያንን ልጆችና የሰማርያን አደጋ ጣዮች ላከበት፤ ከዚህም በኋላ በአገልጋዮቹ በነቢያት እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ራቁ። 5 ‘ሐ’ ነገር ግን ምናሴ ስለሠራቸው ኀጢአቶችና ኢዮአቄም ስላፈሰሰው ንጹሕ ደም፥ ኢየሩሳሌምንም በንጹሕ ደም ስለ ሞላት ከፊቱ ይርቁ ዘንድ የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳ ላይ ነበር። 5 ‘መ’ እግዚአብሔርም ሊያጠፋቸው አልፈለገም ነበር። 6 የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በእርሱ ላይ ወጥቶ ወደ ባቢሎን ይወስደው ዘንድ በሰንሰለት አሰረው። 7 ናቡከደነፆርም ከእግዚአብሔር ቤት ዕቃ አያሌውን አውጥቶ ወደ ባቢሎን ወሰደ፤ በባቢሎንም በጣዖቱ ቤት ውስጥ አኖረው። 8 የቀሩትም የኢዮአቄም ነገሮች፥ ያደረገውም ርኵሰት፥ በእርሱም የተገኘው ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል፤ ኢዮአቄምም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር በጋኖዛን ከተማ ተቀበረ። ልጁም ኢኮንያን ከእርሱ ቀጥሎ ነገሠ። 9 ኢኮንያንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የዐሥራ ስምንት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ከዐሥር ቀን ነገሠ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ። 10 ዓመቱም ባለፈ ጊዜ ንጉሡ ናቡከደነፆር ልኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ የከበረውንም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ከእርሱ ጋር አስወሰደ፤ የአባቱን የኢዮአቄምን ወንድም ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ። 11 ሴዴቅያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አንድ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ። 12 በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ ከነቢዩ ከኤርምያስ ፊት፥ ከእግዚአብሔርም ቃል የተነሣ አላፈረም። 13 ደግሞም በእግዚአብሔር ስም አምሎት በነበረው በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ ወደ እስራኤልም አምላክ ወደ እግዚአብሔር እንዳይመለስ አንገቱን አደነደነ፤ ልቡንም አጠነከረ። 14 የይሁዳም ታላላቅ ሰዎች ካህናቱና የሀገሩም ሕዝብ በአሕዛብ ርኵሰት ሁሉ መተላለፍን አበዙ፤ በኢየሩሳሌምም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት አረከሱ። 15 የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በነቢያቱ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር። 16 እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፥ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፥ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፥ ቃሉንም ያቃልሉ፥ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር። 17 ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጐልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ለንጉሣቸው ለሴዴቅያስም አልራራለትም፤ ደናግሉንም አልማረም፤ ሽማግሌዎቻቸውንም ወሰዳቸው፤ ሁሉንም እግዚአብሔር በእጁ አሳልፎ ሰጠው። 18 የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃ ሁሉ፥ ታላቁንና ታናሹን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት መዝገብ፥ የንጉሡንም ቤት መዝገብ፥ የአለቆቹንም ቤት መዝገብ፥ እነዚህን ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰደ። 19 የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሰ፤ አዳራሾችዋንም በእሳት አቃጠለ፤ መልካሙንም ዕቃዋን ሁሉ አጠፋ። 20 የተረፉትንም ወደ ባቢሎን ማረካቸው፤ የሜዶንም ንጉሥ እስኪነግሥ ድረስ ለንጉሡና ለልጆቹ ባሪያዎች ሆኑ፤ 21 በኤርምያስ አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም፥ ምድሪቱ ሰንበትን በማድረግዋ እስክታርፍ ድረስ፥ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ፥ ሰባ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ፥ ሰንበትን አገኘች። 22 በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ከተፈጸመ በኋላ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ በመንግሥቱም ሁሉ አዋጅ ይነገር ዘንድ በጽሕፈት እንዲህ ሲል አዘዘ፤ 23 “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ እርሱም በይሁዳ ባለችው በኢየሩሳሌም ቤትን እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡም ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይሁን፤ እርሱም ይውጣ።” |