2 ዜና መዋዕል 34 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ( 2ነገ. 22፥1-2 ) 1 ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ። 2 በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም። 3 በነገሠም በስምንተኛው ዓመት ገና ብላቴና ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ ይፈልግ ጀመረ፤ በዐሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኮረብታውና ከዐፀዶቹ፥ ከተቀረጹትና ቀልጠው ከተሠሩት ምስሎች ያነጻ ጀመር። 4 የበዓሊምንም መሠዊያዎች በፊቱ አፈረሰ፤ በላዩም የነበሩትን ኮረብታዎችን ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የተቀረጹትንና ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች ሰባበረ፤ አደቀቃቸውም፤ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብርም ላይ በተናቸው። 5 የካህኖቻቸውንም አጥንት በመሠዊያቸው ላይ አቃጠለ። ይሁዳንና ኢየሩሳሌምንም አነጻ። 6 የምናሴንና የኤፍሬምንም፥ የስምዖንና የንፍታሌምንም ከተሞች፥ በዙሪያቸውም ያለውን ቦታ እንዲሁ አነጻ። 7 መሠዊያዎቹንም አፈረሰ፤ የማምለኪያ ዐፀዶቹንና የተቀረጹትን ምስሎችም አደቀቀ፤ በእስራኤልም ሀገር ሁሉ የኮረብታዎችን መስገጃዎችአጠፋ። ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ። 8 በነገሠም በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ምድሪቱንና የእግዚአብሔርን ቤት ካነጻ በኋላ፥ የሴልያ ልጅ ሳፋን፥ የከተማዪቱም አለቃ መዕሴያ፥ ታሪክ ጸሓፊውም የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአክ የእግዚአብሔርን የአምላኩን ቤት ይጠግኑ ዘንድ ሰደዳቸው። 9 ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኬልቅያስ መጡ፤ ሌዋውያኑም በረኞች ከምናሴና ከኤፍሬም፥ ከአለቆችም፥ ከቀረውም ከእስራኤል ሁሉ፥ ከይሁዳና ከብንያም ሁሉ በኢየሩሳሌምም ከሚኖሩት የሰበሰቡትን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት የቀረበውን ገንዘብ ሰጡት። 10 የእግዚአብሔርንም ቤት በሚሠሩት ላይ ለተሾሙት ሰጡ፤ እነርሱም ይጠግኑና ያድሱ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠሩ ሠራተኞች ሰጡአቸው። 11 የይሁዳ ነገሥታት ላፈረሱት ቤት ሰረገሎች ያደርጉ ዘንድ፥ ለማጋጠሚያም እንጨት፥ የተጠረበውንም ድንጋይ ይገዙ ዘንድ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች ሰጡ። 12 ሰዎቹም ሥራውን በመታመን አደረጉ፤ በእነርሱም ላይ የተሾሙት፥ ሥራውንም የሚያሠሩት ሌዋውያን ከሜራሪ ልጆች ይኤትና አብድያስ፥ ከቀዓትም ልጆች ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን በዜማ ዕቃ ዐዋቂዎች፥ የነበሩ ሁሉ፥ 13 በተሸካሚዎችና ልዩ ልዩ ሥራ በሚሠሩ ላይ ተሾመው ነበር፤ ጸሓፊዎቹና አለቆቹም በረኞቹም ከሌዋውያን ወገን ነበሩ። ካህኑ ኬልቅያስ የሕጉን መጽሐፍ እንደ አገኘ ( 2ነገ. 22፥3-20 ) 14 ወደ እግዚአብሔርም ቤት የቀረበውን ገንዘብ ባመጡ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ እጅ የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ። 15 ኬልቅያስም ጸሓፊውን ሳፋንን፥ “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቼአለሁ” ብሎ ነገረው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። 16 ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ አመጣ፤ ለንጉሡም ዳግመኛ እንዲህ አለው፥ “ወርቁንና ብሩን፥ መባውንም ሁሉ የቤተ እግዚአብሔርን ሥራ ለሚሠሩ ለአገልጋዮችህ በእጃቸው ሰጧቸው። 17 በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን ገንዘብ አፈሰሱ፤ በሥራው ላይ ለተሾሙትና ለሠራተኞቹም በእጃቸው ሰጡ።” 18 ጸሓፊውም ሳፋን ለንጉሡ፥ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጠኝ” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። 19 ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። 20 ንጉሡም ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ አብዶንን፥ ጸሓፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዔሴኢያን፦ 21 “በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ፥ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ስለእኔ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ስለቀሩትም እግዚአብሔርን ጠይቁ” ብሎ አዘዛቸው። 22 ኬልቅያስና እነዚያ ንጉሡ ያዘዛቸው ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቴቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በከተማዪቱ በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ይህንም ነገር ነገሩአት። 23 እርስዋም አለቻቸው፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ 24 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ፥ ማለት ክፉ ነገርን አመጣለሁ፥ 25 በእጃቸው ሥራ ሁሉ ሊያስቈጡኝ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት አጥነዋልና ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም። 26 እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለ ሰማኸው ቃል ልብህ ደንግጦአልና፥ 27 በፊቴም ራስህን አዋርደሃልና፥ በዚህም ስፍራ በሚኖሩበት ላይ ቃሌን በሰማህ ጊዜ ራስህን አዋርደሃልና፥ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 28 እነሆ፥ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም” ያለቻቸውንም ነገር ለንጉሡ አስረዱት። 29 ንጉሡም ላከ፤ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰበ። 30 ንጉሡም፥ የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ በጆሮአቸው አነበበ። 31 ንጉሡም በዐምዱ ቆሞ እግዚአብሔርን ተከትሎ እንዲሄድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩን፥ ሥርዐቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ እንዲጠብቅ፥ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል እንዲያደርግ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ። 32 በኢየሩሳሌምና በብንያምም ሀገር የተገኙትን ሁሉ በዚህ ነገር አማለ። በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ እንደ አባቶቻቸው አምላክ እንደ እግዚአብሔር ቤት ቃል ኪዳን አደረጉ። 33 ኢዮስያስም ከእስራኤል ልጆች ምድር ሁሉ ርኩሱን ሁሉ አስወገደ፤ በእስራኤልም የተገኙትን ሁሉ አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አደረገ። በዘመኑ ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ከመከተል አልራቁም። |