2 ዜና መዋዕል 32 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን ለመውረር እንደ ተነሣ ( 2ነገ. 18፥13-37 ፤ 19፥14-19 ፤ 35-37 ፤ ኢሳ. 36፥1-22 ፤ 37፥8-38 ) 1 ከእነዚህም ነገሮችና ከዚህ እውነት በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ወደ ይሁዳ ገባ፤ በተመሸጉትም ከተሞች ፊት ሰፈረ፤ ሊወስዳቸውም አሰበ። 2 ሕዝቅያስም ሰናክሬም እንደ መጣ፥ ኢየሩሳሌምንም ሊወጋ ፊቱን እንዳቀና አየ፤ 3 ከከተማዪቱ በስተውጭ ያለውን የውኃውን ምንጭ ይደፍኑ ዘንድ ከአለቆቹና ከኀያላኑ ጋር ተማከረ፤ እነርሱም ምክሩን ወደዱ። 4 ብዙ ሰዎችንም ሰበሰበ፥ “የአሦርም ንጉሥ እንዳይመጣና ብዙ ውኃ አግኝቶ እንዳይጠነክር” ብሎ የውኃ ምንጮችንና በከተማዪቱ የሚፈስሱትን ወንዞች ደፈነ። 5 ሕዝቅያስም ሰውነቱን አጽናና፤ የፈረሰውንም ቅጥር ሁሉ ጠገነ፤ በላዩም ግንብ ሠራበት፤ ከእርሱም በስተውጭ ሌላ ቅጥር ሠራ፤ ወደ ዳዊትም ከተማ የሚያወጣውን በር አጠነከረ፤ ብዙም መሣሪያና ጋሻ አዘጋጀ። 6 የጦር አለቆቹንም በሕዝቡ ላይ ሾመ፤ ሁሉንም በሸለቆው በኩል ባለው በከተማዪቱ በር አደባባይ ወደ እርሱ ሰበሰበ፤ እንዲህም ብሎ ልባቸውን አጸና፦ 7 “ጽኑ፥ አይዞአችሁ፤ ከእኛ ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና ከአሦር ንጉሥና ከእርሱ ጋር ካለው ጭፍራ ሁሉ የተነሣ አትፍሩ፤ አትደንግጡም። 8 ከእርሱ ጋር የሥጋ ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳን የሚዋጋልንም አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ተጽናና። 9 ከዚህም በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር በለኪሶ ፊት ሳለ ባሪያዎቹን ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስና በኢየሩሳሌም ወደ ነበሩ ወደ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ሲል ላከ፦ 10 “የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል፦ እናንተ በማን ተማምናችሁ በኢየሩሳሌም ምሽግ ትቀመጣላችሁ? 11 አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል እያለ ለራብ፥ ለጥምና ለሞት አሳልፎ ይሰጣችሁ ዘንድ የሚያሳስታችሁ ሕዝቅያስ አይደለምን? 12 በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ፤ በእርሱም ላይ ዕጠኑ፤ እያለ የይሁዳን ሕዝብና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች አዝዞ፥ የኮረብታውን መስገጃዎችና መሠዊያዎቹን ያፈረሰ ይህ ሕዝቅያስ አይደለምን? 13 እኔና አባቶች በምድር አሕዛብ ሁሉ ያደረግነውን አላወቃችሁምን? የምድርስ ሁሉ አሕዛብ አማልክት ሀገራቸውን ከእጄ ያድኑ ዘንድ በውኑ ተቻላቸውን? 14 አምላካችሁስ ከእጄ እናንተን ለማዳን ይችል ዘንድ አባቶች ካጠፉአቸው ከአሕዛብ አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄ ያድን ዘንድ የቻለ ማን ነው? 15 አሁንም ሕዝቅያስ አያስታችሁ፤ በእነዚህም ቃላት እንድትተማመኑ አያድርጋችሁ፤ አትመኑትም፤ ከአሕዛብና ከመንግሥታት አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄና ከአባቶች እጅ ያድን ዘንድ ማንም አልቻለም፤ ስለዚህም አምላካችሁ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ አይችልም።” 16 ባሪያዎቹም ደግሞ በአምላክ በእግዚአብሔርና በባሪያው በሕዝቅያስ ላይ ሌላ ብዙ ነገር ተናገሩ። 17 ደግሞም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እየተገዳደረ በእርሱም ላይ እየተናገረ፥ “የምድር አሕዛብ አማልክት ሕዝባቸውን ከእጄ ያድኑ ዘንድ እንዳልቻሉ፥ እንዲሁ የሕዝቅያስ አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ያድን ዘንድ አይችልም” የሚል ደብዳቤ ጻፈ። 18 ቅጥሩን እንዲያፈርሱ ከተማዪቱንም እንዲወስዱ፥ በቅጥር ላይ የተቀመጡትን የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ያስፈራቸውና ያስደነግጣቸው ዘንድ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ይጮኽባቸው ነበር። 19 በሰውም እጅ በተሠሩ በምድር አሕዛብ አማልክት ላይ እንደሚናገር መጠን በኢየሩሳሌም አምላክ ላይ ተናገረ። 20 ንጉሡ ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ተግዳሮት ጸለዩ፤ ወደ ሰማይም ጮኹ። 21 እግዚአብሔርም መልአኩን ላከ፤ እርሱም ጽኑዓን ኀያላኑንና መሳፍንቱን አለቆቹንም ከአሦር ንጉሥ ሰፈር አጠፋ። የአሦርም ንጉሥ አፍሮ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩም ቤት በገባ ጊዜ ከወገቡ የወጡት ልጆቹ በዚያ በሰይፍ ገደሉት። 22 እግዚአብሔርም ሕዝቅያስንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ከአሦር ንጉሥ ከስናክሬም እጅና ከሁሉም እጅ አዳናቸው፤ በዙሪያቸውም ካለው ሁሉ አሳረፋቸው። 23 ብዙዎቹም ለእግዚአብሔር መባ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር፤ ለይሁዳም ንጉሥ ለሕዝቅያስ እጅ መንሻ ይሰጡ ነበር፤ እርሱም ከዚህ ነገር በኋላ በሕዝብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ። 24 በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስከ ሞት ድረስ ታመመ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እርሱም ሰማው፤ ምልክትም ሰጠው። 25 ሕዝቅያስ ግን እግዚአብሔር እንደ ሰጠው ቸርነት መጠን አላደረገም፤ ልቡም ኮራ፤ ስለዚህም በእርሱና በይሁዳ፥ በኢየሩሳሌምም ላይ ቍጣ ሆነ። 26 ሕዝቅያስም በኢየሩሳሌም ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ስለ ልቡ ኵራት ሰውነቱን አዋረደ፤ እግዚአብሔርም በሕዝቅያስ ዘመን ቍጣውን አላመጣባቸውም። 27 ለሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀብትና ክብር ነበረው፤ ለብርና ለወርቅም፥ ለከበረው ዕንቍና ለሽቱው፥ ለጋሻውና ውድ ለሆነው ዕቃ ሁሉ ግምጃ ቤቶችን ሠራ። 28 ለእህልና ለወይን ጠጅም ለዘይትም ዕቃ ቤቶች፥ ለልዩ ልዩም እንስሳ ጋጥ፥ ለመንጎችም በረት ሠራ። 29 እግዚአብሔርም እጅግ ብዙ ጥሪት ሰጥቶት ነበርና ከተሞችን ለራሱ ሠራ፤ ብዙም የበግና የላም መንጋ ሰበሰበ። 30 ይህም ሕዝቅያስ የላይኛውን የግዮንን ውኃ ምንጭ ደፈነ፤ በዳዊትም ከተማ በምዕራብ በኩል አቅንቶ አወረደው። ሕዝቅያስም በሥራው ሁሉ ተከናወነ። 31 ነገር ግን የባቢሎን መሳፍንት መልእክተኞች በሀገሩ ላይ ስለ ተደረገው ተአምራት ይጠይቁት ዘንድ ወደ እርሱ በተላኩ ጊዜ እግዚአብሔር ይፈትነውና በልቡ ያለውን ሁሉ ያውቅ ዘንድ ተወው። 32 የሕዝቅያስም የቀሩት ነገሮች፥ ቸርነቱም፥ እነሆ፥ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ በይሁዳና በእስራኤልም ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። 33 ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ልጆች መቃብር በላይኛው ክፍል ቀበሩት፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትም ሁሉ በሞቱ አከበሩት። ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |