2 ዜና መዋዕል 30 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የበዓለ ፋሲካ አከባበር በዘመነ ሕዝቅያስ 1 ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ፋሲካ ያደርጉ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጡ ሕዝቅያስ ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ላከ፤ ደግሞም ወደ ኤፍሬምና ወደ ምናሴ ደብዳቤዎችን ጻፈ። 2 ንጉሡና አለቆቹ በኢየሩሳሌምም ያለ የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ በሁለተኛው ወር ፋሲካውን ያደርጉ ዘንድ ተማከሩ። 3 ካህናቱ በሚበቃ ቍጥር ስላልተቀደሱ፥ ሕዝቡም ገና በኢየሩሳሌም ስላልተሰበሰቡ በጊዜው ያደርጉት ዘንድ አልቻሉም ነበርና። 4 ነገሩም ንጉሡንና ጉባኤውን ሁሉ ደስ የሚያሰኝ ሆነ። 5 እንደ ተጻፈም ብዙዎቹ አላደረጉትም ነበርና የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ፋሲካ በኢየሩሳሌም ያደርጉ ዘንድ እንዲመጡ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ ለእስራኤል ሁሉ አዋጅ እንዲነገር ወሰኑ። 6 እንደ ንጉሡም ትእዛዝ መልእክተኞቹ እንዲህ የሚለውን የንጉሡንና የአለቆቹን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ፈጥነው ሄዱ፥ “የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ወዳመለጠ ቅሬታችሁ እንዲመለስ ወደ አብርሃምና ወደ ይስሐቅ ወደ ያዕቆብም አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ። 7 እናንተም እንደምታዩ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን እንደ በደሉ፥ ለጥፋትም እንደ ሰጣቸው እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ። 8 አሁንም እንደ አባቶቻችሁ አንገታችሁን አታደንድኑ፤ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ስጡ፤ ለዘለዓለምም ወደ ተቀደሰው ወደ መቅደሱ ግቡ፤ ጽኑ ቍጣውንም ከእናንተ እንዲመልስ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ተገዙ። 9 አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና መሓሪ ነውና፥ ወደ እርሱም ብንመለስ ፊቱን ከእኛ አያዞርምና ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁ በማረኩአቸው ፊት ምሕረትን ያገኛሉ፤ ደግሞም ወደዚህች ምድር ይመልሳቸዋል።” 10 መልእክተኞቹም ከከተማ ወደ ከተማ በኤፍሬምና በምናሴ ሀገር እስከ ዛብሎን ሄዱ፤ እነዚያ ግን በንቀት ሳቁባቸው፤ አፌዙባቸውም። 11 ነገር ግን ከአሴርና ከምናሴ፥ ከዛብሎንም አያሌ ሰዎች ሰውነታቸውን አዋረዱ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። 12 ደግሞም አንድ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ፥ በእግዚአብሔርም ቃል የሆነውን የንጉሡንና የአለቆቹን ትእዛዝ ያደርጉ ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ በእነርሱ ላይ ሆነ። 13 በሁለተኛውም ወር የቂጣውን በዓል ያደርጉ ዘንድ በኢየሩሳሌም ብዙ ሕዝብ ተሰበሰቡ፤ እጅግም ታላቅ ጉባኤ ነበረ። 14 ተነሥተውም በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎችና ለጣዖታት የሚያጥኑበትን ዕቃ ሁሉ አስወገዱ፤ በቄድሮንም ወንዝ ጣሉት። 15 በሁለተኛውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን በግ አረዱ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ተዘጋጁ ነጹም። ወደ እግዚአብሔርም ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ። 16 እንደ እግዚአብሔርም ሰው እንደ ሙሴ ሕግ በቦታቸውና በሥርዐታቸው ቆሙ፤ ካህናቱም ከሌዋውያን እጅ የተቀበሉትን ደም ይረጩ ነበር። 17 በጉባኤውም ያልነጹ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን ለእግዚአብሔር ራሳቸውን ላላነጹት ሁሉ የፋሲካውን በግ ያርዱላቸው ነበር። 18 እንደ ትእዛዙም ሳይሆን ከኤፍሬምና ከምናሴ፥ ከይሳኮርና ከዛብሎንም ወገን እጅግ ሰዎች ሳይነጹ ፋሲካውን በሉ። 19 ሕዝቅያስም ስለ እነርሱ እንዲህ ሲል ጸለየ፥ “ምንም እንደ መቅደሱ ማንጻት ባይነጻ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልቡን የሚያቀናውን ሁሉ ቸሩ እግዚአብሔር ይቅር ይበለው።” 20 እግዚአብሔርም ሕዝቅያስን ሰማው፤ ሕዝቡንም አዳናቸው። 21 በኢየሩሳሌምም ተገኝተው የነበሩ የእስራኤል ልጆች በየቀኑ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ የቂጣውን በዓል በታላቅ ደስታ ሰባት ቀን አደረጉ፤ ሌዋውያኑና ካህናቱም በዜማ ዕቃ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። 22 ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር አገልግሎት አስተዋዮች የነበሩትን ሌዋውያንን ሁሉ ያጽናና ነበር። የደኅንነትም መሥዋዕት እያቀረቡ፥ የአባቶቻቸውንም አምላክ እያመሰገኑ ሰባት ቀን በዓል አደረጉ። 23 ጉባኤው ሁሉ እንደ ገና ሰባት ቀን በዓል ያደርጉ ዘንድ ተማከሩ፤ በደስታም እንደ ገና ሰባት ቀን በዓል አደረጉ። 24 ንጉሡ ሕዝቅያስም ስለ ቍርባን ሺህ ወይፈኖችንና ሰባት ሺህ በጎችን ለይሁዳና ለጉባኤው ሰጥቶ ነበር፤ አለቆቹም ሺህ ወይፈኖችንና ዐሥር ሺህ በጎችን ለጉባኤው ሰጥተው ነበር፤ ከካህናቱ እጅግ ብዙ ተቀድሰው ነበርና። 25 የይሁዳም ጉባኤ ሁሉ ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ ከእስራኤልም የመጡ ጉባኤ ሁሉ፥ ከእስራኤልም ሀገር የመጡትና በይሁዳ የኖሩት እንግዶች ደስ አላቸው። 26 በኢየሩሳሌምም ታላቅ ደስታ ሆነ፤ ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ በዓል በኢየሩሳሌም አልተደረገም ነበር። 27 ካህናቱና ሌዋውያኑም ተነሥተው ሕዝቡን ባረኩ፤ ድምፃቸውም ተሰማ፥ ጸሎታቸውም ወደ ቅዱስ ማደሪያው ወደ ሰማይ ዐረገ። |