2 ዜና መዋዕል 29 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ( 2ነገ. 18፥1-3 ) 1 ሕዝቅያስም የሃያ አምስት ዓመት ጐልማሳ በነበረ ጊዜ መንገሥ ጀመረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አብያ ትባል ነበር። 2 አባቱም ዳዊት እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ። የቤተ መቅደስ መንጻት 3 በመንግሥቱም በጸና ጊዜ በመጀመሪያው ወር የእግዚአብሔርን ቤት ደጆች ከፈተ፤ አደሳቸውም። 4 ካህናቱንና ሌዋውያኑንም አስመጣ፤ በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይም ሰበሰባቸው፤ 5 እንዲህም አላቸው፥ “ሌዋውያን ሆይ፥ ስሙኝ፤ ራሳችሁን አንጹ፤ የአባቶቻችሁንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ቀድሱ፤ ርኩስን ነገር ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ። 6 አባቶቻችን ከእግዚአብሔር ርቀዋል፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርገዋል፤ እርሱንም ረስተዋል፤ ፊታቸውንም ከእግዚአብሔር ቤት መልሰዋል፤ ጀርባቸውንም አዙረዋል፤ 7 ደግሞም የእግዚአብሔርን ቤት ደጆች ዘግተዋል፤ መብራቶቹንም አጥፍተዋል፤ በመቅደሱም ውስጥ ለእስራኤል አምላክ አላጠኑም፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አላቀረቡም። 8 “ስለዚህም የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ሆነ፤ በዐይናችሁም እንደምታዩ ለድንጋጤና ለመደነቂያ፥ ለመዘበቻም አሳልፎ ሰጣቸው። 9 እነሆም፥ ስለዚህ አባቶቻችሁ በሰይፍ ወደቁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም፥ ሚስቶቻችሁም የእነርሱ ሀገር ወዳልሆነ ተማረኩ፤ እስከ ዛሬም በዚያ ይኖራሉ። 10 አሁንም የቍጣውን መቅሠፍት ከእኛ እንዲመልስ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን አደርግ ዘንድ በልቤ አስቤአለሁ። 11 አሁንም በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ፥ አገልጋዮቹም ትሆኑ ዘንድ፥ ታጥኑለትም ዘንድ እግዚአብሔር መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ።” 12 ሌዋውያኑም፥ ከቀዓት ልጆች የአሜሳእ ልጅ መኤትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮሔል፥ ከሜራሪም ልጆች የአብዲ ልጅ ቂስና የያሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፥ ከጌድሶንም ልጆች የዛማት ልጅ ዮአክና የዮአክ ልጅ ኢዮአድ፤ 13 ከኤልሳፋንም ልጆች ሳምሪና ኢዮሔል፥ ከአሳፍም ልጆች ዘካርያስና ማታንያስ፤ 14 ከኤማንም ልጆች ኢዮሔልና ሰሜኢ፥ ከኢዱቱንም ልጆች ሰማዕያና ኡዝሔል ተነሡ። 15 ወንድሞቻቸውንም ሰብስበው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ንጉሡ ትእዛዝ የእግዚአብሔርን ቤት ያነጹ ዘንድ ራሳቸውን አነጹ። 16 ካህናቱም ያነጹት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጥ ገቡ፤ በእግዚአብሔርም መቅደስ ያገኙትን ርኩስ ነገር ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ቤት አደባባይ አወጡት። ሌዋውያንም ወስደው ወደ ሜዳ ወደ ቄድሮን ወንዝ ጣሉት። 17 በመጀመሪያውም ወር በመጀመሪያው ቀን ያነጹ ጀመር፤ በዚያውም ወር በስምንተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ወለል ደረሱ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት በስምንት ቀን አነጹ፤ በመጀመሪያውም ወር በዐሥራ ስድስተኛው ቀን ፈጸሙ። 18 ወደ ውስጡም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው፥ “የእግዚአብሔርን ቤት ሁሉ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የኅብስተ ገጹንም ገበታና ዕቃውን ሁሉ አንጽተናል፤ 19 ንጉሡም አካዝ ነግሦ ሳለ በመተላለፉ ያረከሰውን ዕቃ ሁሉ አዘጋጅተናል፤ ቀድሰናልም፤ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ሆነዋል” አሉት። 20 ንጉሡም ሕዝቅያስ ማልዶ ተነሣ፤ የእስራኤልንም ቤት አለቆች ሰበሰበ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ወጣ። 21 ስለ መንግሥቱና ስለ መቅደሱም፥ ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል ለኀጢአት መሥዋዕት ሰባት ወይፈኖች፥ ሰባትም አውራ በጎች፥ ሰባትም የበግ ጠቦቶች፥ ሰባትም አውራ ፍየሎች አመጡ። የአሮንንም ልጆች ካህናቱን፥ “ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ ውጡ” አላቸው። 22 ወይፈኖቹንም አረዱ፤ ካህናቱም ደሙን ተቀብለው በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም አረዱ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ ጠቦቶቹንም አረዱ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት። 23 የኀጢአት መሥዋዕት የሚሆኑትንም አውራ ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፤ እጃቸውንም ጫኑባቸው፤ 24 ካህናቱም አረዱአቸው፤ ንጉሡም የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት ለእስራኤል ሁሉ እንዲደረግ አዝዞ ነበርና ለእስራኤል ሁሉ ማስተስረያ ያደርጉ ዘንድ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ አቀረቡ። 25 ይህንም ትእዛዝ እግዚአብሔር በነቢያቱ እጅ አዝዞአልና እንደ ዳዊትና እንደ ንጉሡ ባለ ራእይ እንደ ጋድ፥ እንደ ነቢዩም እንደ ናታን ትእዛዝ፥ ጸናጽልና በገና፥ መሰንቆም አስይዞ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ፊት አቆመ። 26 ሌዋውያንም የዳዊትን የዜማ ዕቃ ይዘው፥ ካህናቱም መለከቱን ይዘው ቆመው ነበር። 27 ሕዝቅያስም፥ “የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ አሳርጉ” አለ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማሳረግ በተጀመረ ጊዜ የእግዚአብሔር መዝሙር ደግሞ ተጀመረ፤ መለከቱም ተነፋ፤ የእስራኤልም ንጉሥ የዳዊት ዜማ ዕቃ ተመታ። 28 የሚቃጠለውም መሥዋዕት እስኪፈጸም ድረስ ጉባኤው ሁሉ ይሰግዱ ነበር፤ መዘምራኑም ይዘምሩ ነበር፤ መለከተኞችም ይነፉ ነበር። 29 ማቅረቡንም በፈጸሙ ጊዜ ንጉሡ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሁሉ አጐነበሱ፤ ሰገዱም። 30 ንጉሡ ሕዝቅያስና አለቆቹም በዳዊትና በነቢዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ሌዋውያንን አዘዙ። በደስታም አመሰገኑ፤ አጐነበሱም፤ ሰገዱም። 31 ሕዝቅያስም፥ “አሁን እጃችሁን ለእግዚአብሔር አንጽታችሁ ቅረቡ፤ መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጡ” ብሎ ተናገረ። ጉባኤውም መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጡ፤ ልባቸውም የፈቀደ ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አመጡ። 32 ጉባኤውም ያመጡት የሚቃጠል መሥዋዕት ቍጥር ሰባ ወይፈን፥ መቶም አውራ በጎች፥ ሁለት መቶም የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ ይህ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ። 33 የተቀደሱትም ቍጥር ስድስት መቶ በሬዎች፥ ሦስት ሺህም በጎች ነበረ። 34 ነገር ግን ካህናቱ ጥቂቶች ነበሩና የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለመግፈፍ አይችሉም ነበር፤ ስለዚህም ሌዋውያን በቅን ልብ ከካህናት ይልቅ ይቀደሱ ነበርና ሥራው እስኪፈጸም ድረስ፥ ካህናቱም እስኪቀደሱ ድረስ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን ያግዙአቸው ነበር። 35 የሚቃጠለውም መሥዋዕት ከደኅንነቱ መሥዋዕት ስብና ለሚቃጠለውም መሥዋዕት ከሚቀርበው የመጠጥ ቍርባን ጋር ብዙ ነበረ። እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ተዘጋጀ። 36 ሕዝቅያስና ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስላዘጋጀው ነገር ደስ አላቸው። ይህ ነገር በድንገት ተደርጎአልና። |