2 ዜና መዋዕል 26 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያን ዘመነ መንግሥት ( 2ነገ. 14፥21-22 ፤ 15፥1-7 ) 1 የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የዐሥራ ስድስት ዓመት ጐልማሳ የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት። 2 ንጉሥ አባቱም ከአባቶቹ ጋር ከአንቀላፋ በኋላ ዖዝያን ኤላትን ሠራ፤ ወደ ይሁዳም መለሳት። 3 ዖዝያንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የዐሥራ ስድስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ኢዮኮልያስ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 4 አባቱም አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ። 5 እግዚአብሔርንም መፍራት ባስተማረ በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ልብ አደረገ፤ በዘመኑም እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርም ነገሩን አከናወነለት። 6 ወጥቶም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፤ የጌትን ቅጥር፥ የኢያቢስንም ቅጥር፥ የአዛጦንንም ቅጥር አፈረሰ፤ በአዛጦንና በፍልስጥኤማውያንም ሀገር ከተሞችን ሠራ። 7 እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያንና በዓለት ላይ በሚኖሩ ዓረባውያን፥ በምዕዑናውያንም ላይ አጸናው። 8 አሞናውያንም ለዖዝያን ገበሩ፤ እጅግም በርትቶ ነበርና ዝናው እስከ ግብፅ መግቢያ ድረስ ተሰማ። 9 ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማዕዘኑ በርና በሸለቆው በር፥ ቅጥሩም በዞረበት ማዕዘን አጠገብ ግንቦችን ሠርቶ መሸጋቸው። 10 በምድረ በዳውም ግንቦችን ሠራ፤ ብዙ ጕድጓድም ማሰ፤ በቆላውና በደጋው ብዙ እንስሶች ነበሩትና፤ ደግሞም እርሻ ይወድድ ነበርና በተራራማውና በፍሬያማው ስፍራ አራሾችና የወይን አትክልተኞች ነበሩት። 11 ደግሞም ለዖዝያን የሰልፍ ሠራዊት ነበሩት፤ በንጉሡ አለቃ በሐናንያ ትእዛዝ፥ በአለቃው በመዕሤያና በጸሓፊው በኢዮሔል እጅ እንደ ተቈጠሩ ወደ ሰልፍ በየቍጥራቸው ይወጡ ነበር። 12 የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች በሰልፍ ጽኑዓንና ኀያላን የሆኑ ሁሉ ቍጥራቸው ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበረ። 13 ከእነርሱም ጋር ወደ ሰልፍ የሚወጡ ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ሠራዊት ነበሩ፤ እነዚህም ንጉሡን በጠላቱ ላይ የሚያግዙ፥ በታላቅ ኀይል ወደ ሰልፍ የሚወጡ ጽኑዓን ነበሩ። 14 ዖዝያንም ለጭፍራው ሁሉ ጋሻና ጦር፥ ራስ ቍርና ጥሩር፥ ቀስትና የሚወነጭፉትን ድንጋይ አዘጋጀላቸው። 15 በኢየሩሳሌምም በብልሃተኞች እጅ የተሠሩትን ፥ በግንብና በቅጥር ላይ የሚኖሩትን፥ ፍላጻና መርግ የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች አደረገ፤ እስኪበረታም ድረስ እግዚአብሔር በድንቅ ረድቶታልና የመሣሪያዎቹ ዝና እስከ ሩቅ ድረስ ተሰማ። 16 ነገር ግን በበረታ ጊዜ ለጥፋት ልቡ ታበየ፤ አምላኩንም እግዚአብሔርን በደለ፤ በዕጣን መሠዊያውም ላይ ያጥን ዘንድ ወደ መቅደስ ገባ። 17 ካህኑም ዓዛርያስ፥ ከእርሱም ጋር ጽኑዓን የነበሩ ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ተከትለው ገቡ። 18 ንጉሡንም ዖዝያንን እየተቃወሙ፥ “ዖዝያን ሆይ፥ ዕጣን ማጠን ለተቀደሱት ለአሮን ልጆች ለካህናቱ ነው እንጂ ለእግዚአብሔር ታጥን ዘንድ ለአንተ አይገባህም፤ ከእግዚአብሔር ርቀሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ይህም በአምላክ በእግዚአብሔርም ዘንድ ለአንተ ክብር አይሆንህም” አሉት። 19 ዖዝያንም ተቈጣ፤ በመቅደስም የሚያጥንበት ጥና በእጁ ነበረ፤ ካህናቱንም በተቈጣ ጊዜ በካህናቱ ፊት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ ሳለ በግንባሩ ላይ ለምጽ ታየ። 20 ታላቁ ካህን ዓዛርያስ፥ ካህናቱም ሁሉ ተመለከቱት፤ እነሆም፥ በግንባሩ ላይ ለምጽ ነበረ፤ ፈጥነውም አባረሩት፤ እርሱም ደግሞ እግዝአብሔር ቀሥፎት ነበርና ይወጣ ዘንድ ቸኰለ። 21 ንጉሡም ዖዝያን እስኪሞት ድረስ ለምጻም ነበረ፤ ለምጻምም ሆኖ ከእግዚአብሔር ቤት ርቆአልና በተለየ ቤት ይቀመጥ ነበር፤ ልጁም ኢዮአታም በቤተ መንግሥቱ ሆኖ በምድሩ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር። 22 የቀሩትም የፊተኞቹና የኋለኞቹ የዖዝያን ነገሮች በነቢዩ በኢሳይያስ መጽሐፍ ተጽፈዋል። 23 ዖዝያንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ለምጻም ነው ብለዋልና የነገሥታቱ መቃብር ባልሆነ እርሻ ውስጥ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |