2 ዜና መዋዕል 25 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ዘመነ መንግሥት ( 2ነገ. 14፥2-6 ) 1 አሜስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ኢዮዓዲን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 2 በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገርን አደረገ፤ ነገር ግን በፍጹም ልብ አይደለም። 3 መንግሥትም በእጁ በጸናለት ጊዜ ንጉሡን አባቱን የገደሉትን ባሪያዎች ገደለ። 4 እንደ እግዚአብሔር ሕግ ቃል ኪዳን እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔርም፥ “ሰው ሁሉ በገዛ ኀጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች በልጆቻቸው፥ ልጆችም በአባቶቻቸው ፋንታ አይሙቱ” ብሎ እንዳዘዘ ልጆቻቸውን ግን አልገደለም። በኤዶምያስ ላይ የተደረገ ጦርነት ( 2ነገ. 14፥7 ) 5 ንጉሡ አሜስያስም የይሁዳን ሕዝብ ሰበሰበ፤ እንደ እየአባቶቻቸውም ቤቶች አቆማቸው፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ሁሉ የሽህ አለቆችንና የመቶ አለቆችን አደረገ፤ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን ሁሉ ቈጠረ፤ ለሰልፍም የሚወጡ፥ ጋሻና ጦርም የሚይዙ ሦስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎችን አገኘ። 6 ደግሞም ከእስራኤል ዘንድ መቶ ሺህ ጽኑዓን ኀያላን ሰዎችን በመቶ መክሊት ብር ቀጠረ። 7 አንድ የእግዚአብሔር ሰው ግን ወደ እርሱ መጥቶ፥ “ንጉሥ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤልና ከኤፍሬም ልጆች ሁሉ ጋር አይደለምና የእስራኤል ጭፍራ ከአንተ ጋር አይውጣ። 8 ብትሄድ ግን፥ በእነርሱም ማሸነፍን ብታስብ፥ የማጽናትና የመጣል ኀይል ከእግዚአብሔር ዘንድ ነውና እግዚአብሔር በጠላቶችህ ፊት ይጥልሃል” አለው። 9 አሜስያስም የእግዚአብሔርን ሰው፥ “ለእስራኤል ጭፍራ የሰጠሁት መቶ መክሊት ምን ይሁን?” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው፥ “ከዚህ አብልጦ ይሰጥህ ዘንድ ለእግዚአብሔር አይሳነውም” ብሎ መለሰለት። 10 ንጉሡ አሜስያስም ከኤፍሬም ከተሞች የመጡ ጭፍሮች ወደ ስፍራቸው ይመለሱ ዘንድ ለይቶ አሰናበታቸው፤ ስለዚህም ቍጣቸው በይሁዳ ላይ ጸና፤ ወደ ስፍራቸውም በጽኑ ቍጣ ተመለሱ። 11 አሜስያስም በረታ፤ ሕዝቡንም ሰብስቦ ወደ ጨው ሸለቆ ሄደ፤ ከሴይርም ልጆች ዐሥር ሺህ ገደለ። 12 የይሁዳም ልጆች ደግሞ ዐሥር ሺህ ሰዎችን ማረኩ። ወደ ዐለቱም ራስ ላይ አመጡአቸው፤ ከዐለቱም ራስ ላይ ጣሉአቸው፤ ሁሉም ተፈጠፈጡ። 13 አሜስያስ ግን ከእርሱ ጋር ወደ ሰልፍ እንዳይሄዱ ያሰናበታቸው ጭፍሮችም ከሰማርያ ጀምረው እስከ ቤትሮን ድረስ በይሁዳ ከተሞች ላይ አደጋ ጣሉ፤ ከእነርሱም ሦስት ሺህ ገደሉ፤ ብዙም ምርኮ ማረኩ። 14 አሜስያስም የኤዶምያስን ሰዎች ከገደለ በኋላ የሴይርን ልጆች አማልክት አመጣ፤ የእርሱም አማልክት ይሆኑ ዘንድ አቆማቸው፤ በፊታቸውም ይሰግድላቸውና ይሠዋላቸው ነበር። 15 ስለዚህም የእግዚአብሔር ቍጣ በንጉሡ በአሜስያስ ላይ መጣ፤ እንዲህም ሲል ነቢይን ላከበት፥ “ሕዝባቸውን ከአንተ እጅ ያላዳኑትን የአሕዛብን አማልክት ስለምን ፈለግሃቸው?” 16 እርሱም ይህን ሲናገር ንጉሡ አሜስያስ፥ “በውኑ የንጉሡ አማካሪ ልትሆን ሹሜሃለሁን? ቅጣት እንዳያገኝህ ተጠንቀቅ” አለው። ነቢዩም፥ “ይህን አድርገሃልና፥ ምክሬንም አልሰማህምና እግዚአብሔር ሊያጠፋህ እንዳሰበ አወቅሁ” ብሎ ዝም አለ። በይሁዳና በእስርኤል መካከል የተደረገ ጦርነት ( 2ነገ. 14፥8-20 ) 17 የይሁዳም ንጉሥ አሜስያስ ምክር አደረገና፥ “ና፥ እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ” ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ኢዮአስ ላከ። 18 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ፦ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ እንዲህ ሲል ላከ፥ “የሊባኖስ ኵርንችት ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው” ብሎ ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም ዱር አውሬዎች መጥተው ኵርንችቱን ረገጡት። 19 አንተም፦ እነሆ፥ ኤዶምያስን መትቻለሁ ብለህ በልብህ ኰርተሃል፤ በቤትህ ተቀመጥ፤ አንተ ከይሁዳ ጋር ትወድቅ ዘንድ ስለምን መከራን በራስህ ትሻለህ?” 20 የኤዶምያስንም አማልክት ስለ ፈለጉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ዘንድ ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበረና አሜስያስ አልሰማም። 21 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤትሳሚስ ላይ እርስ በርሳቸው ተያዩ። 22 ይሁዳም በእስራኤል ፊት ድል ሆኑ፥ እያንዳንዳቸውም ወደ ድንኳናቸው ሸሹ። 23 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤትሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ። 24 ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤት በአብዲዶም እጅ የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፥ በንጉሡም ቤተ መዛግብት የተገኘውን፥ በመያዣ የተያዙትንም ልጆች ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ። 25 የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከኢዮአስ ሞት በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። 26 የቀሩትም የፊተኞቹና የኋለኞቹ የአሜስያስ ነገሮች፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 27 አሜስያስም እግዚአብሔርን ከመከተል በራቀ ጊዜ በኢየሩሳሌም የዐመፅ መሐላ አደረጉበት፤ ወደ ለኪሶም ኮበለለ፤ በስተኋላውም ወደ ለኪሶ ላኩ፤ በዚያም ገደሉት። 28 በፈረስም ጭነው አመጡት፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት። |