2 ዜና መዋዕል 24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢዮአስ ዘመነ መንግሥት ( 2ነገ. 12፥1-16 ) 1 ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። 2 ኢዮአስም በካህኑ በኢዮአዳ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ። 3 ኢዮአዳም ሁለት ሚስቶችን አጋባው፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 4 ከዚህም በኋላ ኢዮአስ የእግዚአብሔርን ቤት ይጠግን ዘንድ አሰበ። 5 ካህናትንና ሌዋውያንንም ሰብስቦ፥ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ውጡ፤ የአምላካችሁንም ቤት በየዓመቱ ለማደስ የሚበቃ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብን ሰብስቡ፤ ነገሩንም ፈጥናችሁ አድርጉ” አላቸው። ሌዋውያን ግን አላፋጠኑም። 6 ንጉሡ ኢዮአስም አለቃውን ኢዮአዳን ጠርቶ፥ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እስራኤልን በምስክሩ ድንኳን በሰበሰበ ጊዜ እንዲያዋጣ ያዘዘውን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ያመጡ ዘንድ ስለ ምን ሌዋውያንን አልተከታተልህም?” አለው። 7 ጎቶልያ ከሐዲት ነበረችና ልጆችዋም የእግዚአብሔርን ቤት አፍርሰዋልና፤ በእግዚአብሔርም ቤት ተቀድሶ የነበረውን ሁሉ ለበኣሊም ሰጥተዋልና። 8 ንጉሡም ሣጥን ሠርተው በእግዚአብሔር ቤት በር አጠገብ በስተውጭ ያኖሩት ዘንድ አዘዘ። 9 የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ በእስራኤል ላይ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር ያመጡ ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። 10 አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ሰጡ፤ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ አስገቡት። 11 ሣጥኑም በሌዋውያን እጅ ወደ ንጉሡ ሹሞች በደረሰ ጊዜ፥ ብዙ ገንዘብም እንዳለበት ባዩ ጊዜ፥ የንጉሡ ጸሓፊና የሊቀ ካህናቱ ሹም እየመጡ ብሩን ከሣጥን ያወጡ ነበር፤ ሣጥኑንም ደግሞ ወደ ስፍራው ይመልሱት ነበር። እንዲሁም በየቀኑ ያደርጉ ነበር፤ ብዙም ገንዘብ ሰበሰቡ። 12 ንጉሡና ኢዮአዳም በእግዚአብሔር ቤት ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰጡአቸው፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤት የሚጠግኑትን ጠራቢዎችንና አናጢዎችን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት የሚያድሱትን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ይቀጥሩበት ነበር። 13 ሠራተኞችም ሠሩ፤ ሥራውም ሁሉ በእጃቸው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት እንደ ቀድሞው ሥራ መለሱ፤ አጽንተውም አቆሙት። 14 በጨረሱም ጊዜ የተረፈውን ገንዘብ ወደ ንጉሡና ወደ ካህኑ ኢዮአዳ ፊት አመጡ፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር ቤት ዕቃ፥ ለአገልግሎትና ለቍርባን ዕቃ፥ ለጭልፋዎችም፥ ለወርቅና ለብርም ዕቃ አደረጉት። በኢዮአዳም ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት ሁልጊዜ ያቀርቡ ነበር። 15 ኢዮአዳም ሸመገለ፤ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ፤ በሞተም ጊዜ ዕድሜው መቶ ሠላሳ ዓመት ነበረ። 16 ከእስራኤልም ጋር፥ ከእግዚአብሔርና ከቤቱም ጋር መልካም ሠርቶአልና በዳዊት ከተማ ከነገሥታቱ ጋር ቀበሩት። 17 ካህኑ ኢዮአዳም ከሞተ በኋላ የይሁዳ አለቆች ገብተው ለንጉሡ ሰገዱ፤ ንጉሡም ሰማቸው። 18 የአባቶቻቸውንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ትተው ባዕድ አምላክንና ጣዖታትን አመለኩ፤ በዚያም ወራት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቍጣ ወረደ። 19 ወደ እግዚአብሔርም ይመልሱአቸው ዘንድ ነቢያትን ይሰድድላቸው ነበር፤ መሰከሩባቸውም፤ እነርሱ ግን አላደመጡም። 20 የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በኢዮአዳ ልጅ በአዛርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆመና፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? መልካምም አይሆንላችሁም፤ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁ እርሱ ትቶአችኋል” አላቸው። 21 ወደ እርሱም ሮጡ በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ደበደቡት። 22 እንዲሁም ንጉሡ ኢዮአስ አባቱ ኢዮአዳ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፤ ልጁንም አዛርያስን አስገደለው፤ እርሱም ሲሞት፥ “እግዚአብሔር ይየው፤ ይፍረደውም” አለ። 23 ዓመቱም ካለፈ በኋላ የሶርያውያን ሠራዊት መጡበት፤ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌምም መጥተው ከሕዝቡ መካከል የሕዝቡን አለቆች ሁሉ አጠፉ፤ ምርኮአቸውንም ሁሉ ለደማስቆ ንጉሥ ላኩ። 24 የሶርያውያንም ሠራዊት ቍጥር ጥቂት ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ብዙውንና ጠንካራውን ሠራዊት አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው፤ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ዘንግተዋልና። በኢዮአስም ላይ ፈረደበት። 25 ከእርሱም ዘንድ አልፈው ከሄዱ በኋላ እጅግ ታሞ ሳለ ተዉት፤ የገዛ ባሪያዎቹም ስለ ካህኑ ስለ ኢዮአዳ ልጅ ደም ተበቅለው በአልጋው ላይ ገደሉት፤ ሞተም፤ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ነገር ግን በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም። 26 የገደሉትም የአሞናዊቱ የሰማት ልጅ ዘቡድ፥ የሞዓባዊቱም የሰማሪት ልጅ ኢዮዛብድ ነበሩ። 27 የልጆቹና በእርሱ ላይ የተደረገው ነገር፥ የእግዚአብሔርንም ቤት ማደሱ፥ እነሆ በነገሥታቱ የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። ልጁም አሜስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |