2 ዜና መዋዕል 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ንጉሥ ኢዮራም ( 2ነገ. 8፥17-24 ) 1 ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 2 ለእርሱም የኢዮሣፍጥ ልጆች አዛርያስ፥ ኢይሔል፥ ዘካርያስ፥ ዔዛርያስ፥ ሚካኤል፥ ሰፋጥያስ የሚባሉ ስድስት ወንድሞች ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ። 3 አባታቸውም ብዙ ስጦታ፥ ብርና ወርቅ፥ የከበረም ዕቃ፥ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሰጣቸው፤ መንግሥቱን ግን የበኵር ልጁ ስለሆነ ለኢዮራም ሰጠው። 4 ኢዮራምም በአባቱ መንግሥት ላይ ተነሥቶ በጸና ጊዜ ወንድሞቹን ሁሉ፥ ሌሎችንም የእስራኤልን መሳፍንት በሰይፍ ገደለ። 5 ኢዮራምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ። 6 የአክዓብንም ልጅ አግብቶ ነበርና የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ። 7 ነገር ግን ከዳዊት ጋር ስላደረገው ቃል ኪዳን፥ ለእርሱና ለልጆቹም በዘመናት ሁሉ መብራትን ይሰጠው ዘንድ ስለ ሰጠው ተስፋ እግዚአብሔር የዳዊትን ቤት ያጠፋ ዘንድ አልወደደም። 8 በእነዚያም ዘመናት የኤዶምያስ ሰዎች በይሁዳ ላይ ዐመፁ፤ ለራሳቸውም ንጉሥ አነገሡ። 9 ኢዮራምም ከአለቆቹና ከሰረገሎቹ ሁሉ ጋር ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሰረገሎቹን አለቆች ከብበው የነበሩትን የኤዶምያስ ሰዎችን መታ፤ ሕዝቡም ወደ ድንኳናቸው ሸሹ። 10 ኤዶምያስ ግን በይሁዳ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፀ፤ በዚያም ዘመን ልብና ደግሞ በእርሱ ላይ ዐመፀ፤ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ትቶ ነበርና። 11 ደግሞም በይሁዳ ተራሮች ላይ መስገጃዎችን ሠራ፤ በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን እንዲያመነዝሩ አደረጋቸው፤ የይሁዳንም ሰዎች አሳታቸው። 12 ከነቢዩም ከኤልያስ እንዲህ የሚል ጽሕፈት መጣበት፥ “የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በአባትህ በኢዮሣፍጥ መንገድ፥ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህምና፥ 13 በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ግን ሄደሃልና፥ የአክዓብም ቤት እንዳደረገ ይሁዳንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን እንዲያመነዝሩ አድርገሃልና፥ ከአንተም የሚሻሉትን የአባትህን ቤት ወንድሞችህን ገድለሃልና፥ 14 እነሆ፥ እግዚአብሔር ሕዝብህንና ልጆችህን፥ ሚስቶችህንም፥ ያለህንም ንብረት ሁሉ በታላቅ መቅሠፍት ይቀሥፋል። 15 አንተም ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀትህ በየዕለቱ እስኪወጣ ድረስ በክፉ የአንጀት ደዌ ትታመማለህ።” 16 እግዚአብሔርም ፍልስጥኤማውያንንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩትን የዓረብያን ሰዎች በኢዮራም ላይ አስነሣ። 17 ወደ ይሁዳም ወጡ፤ በረቱባቸውም፤ የንጉሡንም ቤት ዕቃ ሁሉ፥ ወንዶች ልጆቹንም፥ ሴቶች ልጆቹንም ወሰዱ፤ ከታናሹም ልጅ ከአካዝያስ በቀር ልጅ አልቀረለትም። 18 ከዚህም ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር መድኀኒት በማይገኝለት ደዌ አንጀቱን ቀሠፈው። 19 ከቀንም ወደ ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀቱ ወጣ፤ በክፉም ደዌ ሞተ። ሕዝቡም ለአባቶቹ ያደርገው እንደ ነበረ ለእርሱ የመቃብር ወግ አላደረገም። 20 መንገሥም በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ፤ ማንም ሳያዝንለት ሄደ፤ በዳዊትም ከተማ እንጂ በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም። |