2 ዜና መዋዕል 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሳፍጥ ዘመነ መንግሥት 1 ከአሳም በኋላ ልጁ ኢዮሳፍጥ ነገሠ፤ ኢዮሳፍጥም በእስራኤል ላይ ጠነከረ። 2 በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ሠራዊቱን አኖረ፤ በይሁዳም ሀገር፥ አባቱም አሳ በወሰዳቸው በኤፍሬም ከተሞች መሳፍንቱን አስቀመጠ። 3 እግዚአብሔርም ከኢዮሳፍጥ ጋር ነበረ፤ በፊተኛዪቱም በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄዶአልና፥ ጣዖትንም አልፈለገምና፤ 4 ነገር ግን የአባቱን አምላክ ፈለገ፤ በአባቱም ትእዛዝ ሄደ፤ በእስራኤልም ሥራ አይደለም። 5 እግዚአብሔርም መንግሥቱን በእጁ አጸና፤ ይሁዳም ሁሉ እጅ መንሻ ለኢዮሳፍጥ አመጣ፤ እጅግም ብዙ ብልጥግናና ክብር ሆነለት። 6 ልቡም በእግዚአብሔር መንገድ ከፍ ከፍ አለ፤ የኮረብታውን መስገጃዎችና የማምለኪያ አፀዱንም ከይሁዳ አስወገደ። 7 በነገሠም በሦስተኛው ዓመት በይሁዳ ከተሞች ያስተምሩ ዘንድ መሳፍንቱንና ኀያላኑን ሰዎች አብድያስን፥ ዘካርያስን፥ ናትናኤልን፥ ሚኪያስን ላከ። 8 ከእነርሱም ጋር ሌዋውያንን ሸማያን፥ ነታንያን፥ ዛባድያን፥ አሣሄልን፥ ሰሚራሞትን፥ ዮናታንን፥ አዶንያስን፥ ጦብያን፥ ጦባዶንያስን ከእነርሱም ጋር ካህናቱን ኤሊሳማንና ኢዮራምን ላከ። 9 እነርሱም የእግዚአብሔርን የሕጉን መጽሐፍ ይዘው በይሁዳ ያስተምሩ ነበር፤ ወደ ይሁዳም ከተሞች ሁሉ ተመላልሰው ሕዝቡን አስተማሩ። 10 በይሁዳም ዙሪያ በነበሩ የምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ድንጋጤ ሆነ፤ ከኢዮሳፍጥም ጋር አልተዋጉም። 11 ከፍልስጥኤማውያንም ለኢዮሳፍጥ እጅ መንሻና የብር ግብር ያመጡ ነበር፤ ዐረባውያንም ደግሞ ከመንጎቻቸው ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ በጎችንና ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ ፍየሎችን ያመጡለት ነበር። 12 ኢዮሳፍጥም እየበረታና እጅግም እየከበረ ሄደ፤ በይሁዳም ግንቦችንና የተመሸጉ ከተሞችን ሠራ። 13 በይሁዳም ከተሞች ብዙ ሥራ ሠራ፤ በኢየሩሳሌምም ጽኑዓን ኀያላን ሰልፈኞች ነበሩት። 14 ቍጥራቸውም እንደ አባቶቻቸው ቤት ይህ ነበረ፤ ከይሁዳ ሻለቆች አለቃው ዓድናስ፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኀያላን ሰዎች ነበሩ፤ 15 ከእርሱም በኋላ አለቃው ኢዮአናን፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ 16 ከእርሱም በኋላ እግዚአብሔርን የሚያገለግል የዝክሪ ልጅ ማስያስ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኀያላን ሰዎች ነበሩ። 17 ከብንያምም ጽኑዕ ኀያል የነበረው ኤሊያዳ፥ ከእርሱም ጋር ቀስት የሚገትሩ፥ ወንጭፍ የሚወነጭፉ ሁለት መቶ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ 18 ከእርሱም በኋላ ዮዛባድ፥ ከእርሱም ጋር ለሰልፍ የተዘጋጁ መቶ ሰማንያ ሺህ ሰዎች ነበሩ። 19 ንጉሡ በተመሸጉ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ካኖራቸውም ሌላ እነዚህ ንጉሡን ያገለግሉ ነበር። |