2 ዜና መዋዕል 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ንጉሥ አብያ ከኢዮርብዓም ጋር ያደረገው ጦርነት ( 1ነገ. 15፥1-8 ) 1 ንጉሡም ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ። 2 ሦስት ዓመትም በኢየሩሳሌም ነገሠ፤ የእናቱም ስም መዓካ ነበረ፤ የገባዖን ሰው የኡርኤል ልጅ ነበረች። በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ሰልፍ ነበረ። 3 አብያም የተመረጡትን አራት መቶ ሺህ ኀያላን ሰልፈኞች ይዞ ወደ ሰልፍ ወጣ፤ ኢዮርብዓምም የተመረጡትን ስምንት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኀያላን ሰዎች ይዞ በእርሱ ላይ ተሰለፈ። 4 አብያም በኤፍሬም ተራራ ባለው በሳምሮን ተራራ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ፥ “ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ 5 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ መንግሥትን ለዳዊትና ለልጆቹ በጨው ቃል ኪዳን ለዘለዓለም እንደ ሰጠ በውኑ አታውቁምን? 6 የዳዊት ልጅ የሰሎሞን አገልጋይ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን ተነሥቶ በጌታው ላይ ዐመፀ። 7 ክፉዎች ሰዎችና የሕግ ተላላፊዎች ልጆችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሮብዓም ሕፃን በነበረና በልቡ ድፍረት ባልነበረው ጊዜ፥ ሊቋቋመውም ባልቻለበት ጊዜ፥ በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ላይ በረታበት። 8 አሁንም በዳዊት ልጆች እጅ የሚሆነውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ልትቋቋሙ እንዲህ ትላላችሁ። እናንተም እጅግ ታላቅ ሕዝብ ናችሁ፥ ኢዮርብዓምም አማልክት አድርጎ የሠራላችሁ የወርቅ እንቦሶች ከእናንተ ጋር ናቸው። 9 የአሮንን ልጆች የእግዚአብሔርን ካህናትና ሌዋውያን አላሳደዳችሁምን? ከምድርም አሕዛብ ሁሉ ለራሳችሁ ካህናትን አላደረጋችሁምን? አንድ ወይፈንና ሰባት አውራ በጎችን ይዞ ራሱን ይቀድስ ዘንድ የሚመጣ ሁሉ አማልክት ላልሆኑት ለእነዚያ ካህን ይሆናል። 10 እኛ ግን አምላካችን እግዚአብሔርን አልተውነውም፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች የአሮን ልጆች ካህናቱና ሌዋውያኑ በየሰሞናቸው ያገለግሉታል። 11 በየጥዋቱና በየማታውም ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ጣፋጩን ዕጣን ያሳርጋሉ፤ የገጹንም ኅብስት በንጹሕ ገበታ ላይ፥ የወርቁን መቅረዝና ቀንዲሎቹንም ማታ ማታ እንዲያበሩ ያዘጋጃሉ፤ እኛም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንጠብቃለን፤ እናንተ ግን ትታችሁታል። 12 እነሆም፥ እግዚአብሔር በእኛ ላይ አለቃ ነው፤ መለከቱንም የሚነፉ ካህናቱ ከእኛ ጋር ናቸው፤ በእናንተም ላይ ይጮኻሉ። የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አይበጃችሁምና ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር አቷጉ።” 13 ኢዮርብዓም ግን በስተኋላቸው ይመጣባቸው ዘንድ ድብቅ ጦር አዞረባቸው፤ እነርሱ በይሁዳ ሰፈር ፊት ሳሉ ድብቅ ጦሩ በስተኋላቸው ከበባቸው። 14 የይሁዳም ሰዎች ወደ ኋላቸው በተመለከቱ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰልፉ በፊታቸውና በኋላቸው ነበረ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ፤ ካህናቱም መለከቱን ነፉ። 15 የይሁዳም ሰዎች ጮኹ፤ የይሁዳም ሰዎች በጮኹ ጊዜ እግዚአብሔር ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በይሁዳ ንጉሥ በአብያና በሕዝቡ ፊት መታቸው። 16 የእስራኤልም ልጆች ከይሁዳ ሰዎች ፊት ሸሹ፤ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። 17 አብያና ሕዝቡም ታላቅ አመታት መቱአቸው፤ ከእስራኤልም አምስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች ተገድለው ወደቁ። 18 በዚያም ጊዜ የእስራኤል ልጆች ተዋረዱ፤ የይሁዳም ልጆች በአባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ታምነው ነበርና አሸነፉ። 19 አብያም ኢዮርብዓምን ተከትሎ አሳደደው፤ ከእርሱም ከተሞቹን ቤቴልንና መንደሮችዋን፥ ይሳናንና መንደሮችዋን፥ ዔፍሮንንና መንደሮችዋን ወሰደ። 20 ኢዮርብዓምም ከዚያ በኋላ በአብያ ዘመን አልበረታም፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው፤ ሞተም። 21 አብያም ጸና፤ ዐሥራ አራት ሚስቶችንም አገባ፤ ሃያ ሁለትም ወንዶች ልጆችንና ዐሥራ ስድስት ሴቶች ልጆችን ወለደ። 22 የአብያም የቀረው ነገርና አካሄዱ የተናገራቸውም ቃሎች በነቢዩ በአዶ መጽሐፍ ተጽፈዋል። |