2 ዜና መዋዕል 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሰማያ የትንቢት ቃል ( 1ነገ. 12፥21-24 ) 1 ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ እስራኤልን ወግተው መንግሥቱን ወደ ሮብዓም ይመልሱ ዘንድ ከይሁዳና ከብንያም ቤት የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ሰልፈኞች ጐልማሶችን ሰበሰበ። 2 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሰማያ እንዲህ ሲል መጣ፦ 3 “ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፥ በይሁዳና በብንያምም ላሉት ለእስራኤል ሁሉ፦ 4 ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፤ ወንድሞቻችሁንም አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ’ ብለህ ንገራቸው።” የእግዚአብሔርንም ቃል ሰሙ፤ በኢዮርብዓምም ላይ ከመሄድ ተመለሱ። 5 ሮብዓምም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሠራ። 6 በይሁዳና በብንያም ያሉትንም የተመሸጉትን ከተሞች፥ ቤተ ልሔምን፥ ኤጣምን፥ ቴቁሔን፤ 7 ቤተሱራን፥ ሱላኮን፥ ዓዶላምን፥ 8 ጌትን፥ መሪሳን፥ ዚፍን፥ 9 አዶራይምን፥ ለኪስን፥ ዓዚቃን፤ 10 ሶርዓን፥ ኤሎንን፥ ኬብሮንን ሠራ። 11 ምሽጎቹንም አጠነከረ፤ አለቆችንም አኖረባቸው፤ ምግቡንም፥ ዘይቱንም፥ የወይን ጠጁንም አከማቸባቸው። 12 በከተሞቹ ሁሉ አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦርን አኖረ፤ ከተሞቹንም እጅግ አጠነከራቸው፤ ይሁዳና ብንያምም የእርሱ ወገን ነበሩ። 13 በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ የነበሩ ካህናትና ሌዋውያን ከየሀገራቸው ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። 14 የእግዚአብሔርም ካህናት እንዳይሆኑ ኢዮርብዓምና ልጆቹ አስለቅቀዋቸው ነበርና ሌዋውያን መሰምሪያቸውን ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 15 እርሱ ግን ለኮረብታው መስገጃዎች፥ ከንቱ ለሆኑ ጣዖታቱም፥ ኢዮርብዓም ለሠራቸው እንቦሶችም ካህናትን አቆመ። 16 ደግሞም ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልባቸውን የሰጡ ሁሉ እነርሱን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 17 ሦስት ዓመትም በዳዊትና በሰሎሞን መንገድ ይሄድ ነበርና ሦስት ዓመት የይሁዳን መንግሥት አበረቱ፤ የሰሎሞንንም ልጅ ሮብዓምን አጸኑ። 18 ሮብዓምም የዳዊትን ልጅ የኢያሪሙትን ሴት ልጅ ሞላትን አገባ፤ እናቷም የእሴይ ልጅ የኤልያብ ልጅ አቢካኤል ነበረች። 19 እርስዋም የዑስን፥ ሰማርያንና፥ ዘሃምን ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 20 ከእርስዋም በኋላ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን አገባ፤ እርስዋም አብያን፥ ኢያቲን፥ ዚዛን፥ ሰሎሚትን ወለደችለት። 21 ሮብዓምም ከሚስቶቹና ከቁባቶቹ ሁሉ ይልቅ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን ወደደ፤ ዐሥራ ስምንትም ሚስቶችና ስድሳ ቁባቶች ነበሩት፤ ሃያ ስምንት ወንዶችና ስድሳ ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 22 ሮብዓምም ያነግሠው ዘንድ አስቦአልና የመዓካን ልጅ አብያን በወንድሞቹ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው። 23 ብልሃተኛም ሆነ፤ ልጆቹንም ሁሉ በይሁዳና በብንያም ሀገር ሁሉ በምሽጉ ከተሞች ሁሉ ከፋፈላቸው፤ ብዙም ምግብ ሰጣቸው፤ ብዙም ሚስቶች ፈለገላቸው። |