2 ዜና መዋዕል 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዐሥሩ ነገደ እስራኤል እንደ ዐመፁ ( 1ነገ. 12፥1-20 ) 1 እስራኤልም ሁሉ ያነግሡት ዘንድ ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ። 2 የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ሸሽቶ በግብፅ ይኖር ነበርና ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮርብዓም ከግብፅ ተመለሰ። 3 ልከውም ጠሩት፤ ኢዮርብዓምና እስራኤልም ሁሉ ወደ ሮብዓም መጥተው እንዲህ አሉት፦ 4 “አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቅልልልን፥ እኛም እንገዛልሃለን።” 5 እርሱም፥ “ሂዱ ከሦስት ቀን በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ” አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ። 6 ንጉሡም ሮብዓም፥ “ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድን ነው?” ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወት ሳለ በፊቱ ይቆሙ የነበሩትን ሽማግሌዎች ሰበሰበ። 7 እነርሱም፥ “በዚች ዕለት ለዚህ ሕዝብ ቸርነት ብታደርግላቸው፥ ደስም ብታሰኛቸው፥ መልካም ነገርንም ብትናገራቸው፥ ሁልጊዜ አገልጋዮች ይሆኑልሃል” ብለው ተናገሩት። 8 እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ነገር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። 9 እርሱም፥ “አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድን ነው?” አላቸው። 10 ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች፥ “አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አንተ ግን አቅልልልን ለሚሉህ ሕዝብ፦ ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤ 11 አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው” ብለው ነገሩት። 12 ንጉሡም፥ “በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ” ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ። 13 ንጉሡም ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው፤ ንጉሡም ሮብዓም የሽማግሌዎቹን ምክር ትቶ፦ 14 “አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፤ እኔ ግን እጨምርበታለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” ብሎ እንደ ብላቴኖቹ ምክር ተናገራቸው። 15 እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአኪያ ቃል ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም የተናገረውን ቃሉን እንዲያጸና ለውጡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም። 16 ንጉሡ ስላልሰማቸው ሕዝቡ፥ “በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ምን ርስት አለን? እስራኤል ሆይ፥ ወደ እየድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ፥ አሁን ቤትህን ተመልከት” ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እስራኤልም ሁሉ ወደ እየድንኳኖቻቸው ሄዱ። 17 በይሁዳ ከተሞች የተቀመጡት የእስራኤል ሰዎች ግን ሮብዓምን በላያቸው አነገሡ። 18 ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶራምን ወደ እነርሱ ላከው፤ የእስራኤልም ልጆች በድንጋይ ወገሩት፤ ሞተም፤ ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሰረገላው ወጣ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ። 19 እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከዳዊት ቤት ሸፈተ። |