2 ዜና መዋዕል 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሰሎሞን ጥበብን ከእግዚአብሔር እንደ ለመነ ( 1ነገ. 3፥1-15 ) 1 የዳዊት ልጅ ሰሎሞንም በመንግሥቱ በረታ፤ አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረ፤ እጅግም አከበረው፤ አገነነውም። 2 ሰሎሞንም ለእስራኤል ሁሉ፥ ለሻለቆች ለመቶ አለቆችም፥ ለፈራጆችም፥ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ ለነበሩ መሳፍንት ሁሉ፥ ለአባቶች ቤቶች አለቆች ሁሉ ተናገረ። 3 ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእግዚአብሔር የምስክር ድንኳን በዚያ ነበረና በገባዖን ወዳለው የኮረብታው መስገጃ ሄዱ። 4 ዳዊት ግን የእግዚአብሔርን ታቦት ከቂርያትይዓሪም አወጣት። ለእርሷ በኢየሩሳሌም ድንኳን አዘጋጅቶላት ነበርና። 5 የሆርም ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የናስ መሠዊያ በዚያ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ነበረ፤ ሰሎሞንና የእስራኤልም ጉባኤ የእግዚአብሔርን ታቦት ይፈልጓት ነበር። 6 ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በድንኳኑ አጠገብ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጣ፤ በዚያም አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። 7 በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ለሰሎሞን ታየው፥ “የምሰጥህን ከእኔ ለምን” አለው። 8 ሰሎሞንም እግዚአብሔርን አለው፥ “ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ምሕረትን አድርገሃል፤ በእርሱም ፋንታ አንግሠኸኛል። 9 አሁንም አቤቱ አምላኬ፥ ቍጥሩ እንደ ምድር አሸዋ በሆነው በብዙ ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛልና ስምህ የታመነ ይሁን። 10 አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት እወጣና እገባ ዘንድ ጥበብንና ማስተዋልን ስጠኝ፤ በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ መፍረድ የሚቻለው የለምና።” 11 እግዚአብሔርም ሰሎሞንን አለው፥ “ይህ በልብህ ነበረና፥ ባለጠግነትን፥ ሀብትን፥ ክብርን፥ የጠላቶችህንም ነፍስ፥ ረጅምም ዕድሜን አልለመንህም፤ ነገር ግን ባነገሥሁህ በሕዝቤ ላይ ትፈርድ ዘንድ ጥብብንና ማስተዋልን ለራስህ ለምነሃል። 12 ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥሃለሁ። ካንተ በፊት ለነበሩ ነገሥታት ያልተሰጠውን፥ ከአንተም በኋላ ለሚነሡ የማይሰጠውን ብልፅግናን፥ ገንዘብንና ክብርን እሰጥሃለሁ።” 13 ሰሎሞንም በገባዖን ካለው ኮረብታ ከምስክሩ ድንኳን ፊት ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ። የሰሎሞን ብልጽግና ( 1ነገ. 10፥26-29 ) 14 ሰሎሞንም ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፤ አንድ ሺህ አራት መቶ ሰረገሎች፥ ዐሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሰረገሎች ከተሞችም አስቀመጣቸው። ሕዝቡም ከንጉሡ ጋር በኢየሩሳሌም ነበሩ። 15 ንጉሡም ብሩንና ወርቁን፥ በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ፥ የዝግባንም እንጨት በብዛት በቆላ እንደሚገኝ ሾላ በይሁዳ አኖረ። 16 የሰሎሞን ፈረሶች መምጫ ከግብፅና ከቴቁሄ ምድር ነበር። በዋጋ ገዝተው ከቴቁሄ የሚያመጡአቸውም ከሀገር ሽማግሌዎች የሆኑ የሰሎሞን ነጋዴዎች ነበሩ። 17 ሄደውም ከግብፅ አንድ ሰረገላ በስድስት መቶ ብር፥ አንድንም ፈረስ በመቶ አምሳ ሰቅል ብር አመጡ፤ እንዲሁም ለኬጢያውያንና ለሦርያ ነገሥታት ሁሉ በየተራቸው ያመጡላቸው ነበር። |