1 ዜና መዋዕል 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እስራኤልም ሁሉ ስለ ኀጢአታቸው ወደ ባቢሎን ከተማረኩ በኋላ፥ በየትውልዳቸው ተቈጠሩ፤ እነሆም በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። 2 በእስራኤል ከተሞችና በአውራጃዎቻቸው መጀመሪያ የተቀመጡ ካህናት፥ ሌዋውያንም፥ አገልጋዮችም ነበሩ። 3 ከይሁዳ ልጆችና ከብንያም ልጆች፥ ከኤፍሬምና ከምናሴ ልጆች በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። 4 ከይሁዳ ልጅ ከፋሬስ ልጆች የባኔ ልጅ የአምሪ ልጅ የዖምሪ ልጅ የዓሚሁድ ልጅ ዑታይ ደግሞ ተቀመጠ። 5 ከሴሎናውያንም በኵሩ ዓሣያና ልጆቹ። 6 ከዛራም ልጆች ኢያሄልና ወንድሞቻቸው፥ ስድስት መቶ ዘጠና። 7 ከብንያምም ልጆች የሐስኑአ ልጅ የሆዳይዋ ልጅ የሜሱላም ልጅ ሰሎ፤ 8 የይሮሐም ልጅ ኢያብናአ፤ የሚክሪ ልጅ የኦዚ ልጅ ኤላ፤ የበንያስ ልጅ የራጉኤል ልጅ የሰፋጥያስ ልጅ ሜሱላም፤ 9 በየትውልዳቸውም ወንድሞቻቸው ዘጠኝ መቶ አምሳ ስድስት ነበሩ፤ እነዚህ ሰዎች ሁሉ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ነበሩ። 10 ከካህናቱም ዮዳኤ፥ ዮአሪብ፥ ያኪን፤ 11 የእግዚአብሔርም ቤት አለቃ የአኪጦብ ልጅ፥ የመራዩት ልጅ፥ የሳዶቅ ልጅ፥ የሜሱላም ልጅ የኬልቅያስ ልጅ ዓዛርያስ፤ 12 የመልክያ ልጅ፥ የጳስኮር ልጅ፥ የይሮሐም ልጅ፥ አዳያ፤ የኤሜር ልጅ የምስልሞት ልጅ፥ የሜሱላም ልጅ፥ የኤሕዜራ ልጅ፥ የዓዴኤል ልጅ መዕሣይ፤ 13 የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች ወንድሞቻቸው ሺህ ሰባት መቶ ስድሳ ነበሩ፤ ለእግዚአብሔር ቤትም ማገልገል ሥራ እጅግ ብቁዎች ሰዎች ነበሩ። 14 ከሌዋውያንም ልጆች ከሜራሪ ልጆች የአሳብያ ልጅ፥ የዓዝሪቃም ልጅ፥ የአሱብ ልጅ ሸማያ፤ 15 በቀባቃር፥ ኤሬስ፥ ጋላል፥ የአሳፍ ልጅ የዝክሪ ልጅ የሜካ ልጅ ማታንያስ፤ የኤዶታም ልጅ የጋላል ልጅ የሰማያ ልጅ አብድያ፤ 16 በነጦፋውያንም መንደሮች የተቀመጠው የሕልቃና ልጅ የአሳ ልጅ በራክያ። 17 በረኞችም ሰሎም፥ ዓቁብ፥ ጤልሞን፥ አሒማን፥ ወንድሞቻቸውም ነበሩ፤ ሰሎምም አለቃ ነበረ። 18 እስከዛሬም ድረስ በንጉሥ በር በምሥራቅ በኩል ነበሩ፤ ለሌዊ ልጆች ሰፈር በረኞች ነበሩ። 19 የቆሬም ልጅ የአብያሳፍ ልጅ የቆሬ ልጅ ሰሎም ከአባቱ ቤት የነበሩ ወንድሞቹ ቆሬያውያን በማገልገል ሥራ ላይ ነበሩ፤ የድንኳኑንም መድረክ ይጠብቁ ነበር። አባቶቻቸውም የእግዚአብሔርን ሰፈር መግቢያ ይጠብቁ ነበር። 20 አስቀድሞም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ አለቃቸው ነበረ። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ። 21 የሜሱላም ልጅ ዘካርያስ የምስክሩ ድንኳን ደጅ በረኛ ነበረ። 22 የመድረኩ በረኞች ይሆኑ ዘንድ የተመረጡ እነዚህ ሁሉ ሁለት መቶ ዐሥራ ሁለት ነበሩ። እነዚህ በመንደሮቻቸው በየትውልዳቸው ተቈጠሩ። ዳዊትና ነቢዩ ሳሙኤል ታማኝነታቸውን አይተው በሥራቸው አቆሙአቸው። 23 እነርሱና ልጆቻቸውም በእግዚአብሔር ቤት በድንኳኑ ደጆች ላይ በረኞች ነበሩ። 24 በአራቱ ማዕዘኖች፥ በምሥራቅ፥ በምዕራብ፥ በሰሜን፥ በደቡብ በሮች ነበሩ። 25 ወንድሞቻቸውም በመንደሮቻቸው ሆነው፥ በየሰባቱ ቀን ከእነርሱ ጋር ሊሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይገቡ ነበር። 26 እነዚህ አራቱ ኀያላን ሰዎች ለአራቱ በሮች ኀላፊዎች ነበሩ። ሌዋውያንም በእግዚአብሔር ቤት ባሉ ጓዳዎችና ቤተ መዛግብት ላይ የተሾሙ ነበሩ። 27 የእግዚአብሔርንም ቤት መክፈቻ የሚይዙ፥ ጥዋት ጥዋትም ደጆቹን የሚከፍቱ እነርሱ ነበሩና። 28 ዕቃውንም በቍጥር ያገቡና ያወጡ ነበርና ከእነዚህ አንዳንዶቹ በማገልገያው ዕቃ ላይ ሹሞች ነበሩ። 29 ከእነርሱ አንዳንዶቹ በአገልግሎቱ ዕቃዎች በመቅደሱ ዕቃ ሁሉ፥ በመልካሙም ዱቄት፥ በወይን ጠጁም፥ በዘይቱም፥ በዕጣኑም፥ በሽቱውም ላይ ሹሞች ነበሩ። 30 ከካህናቱም ልጆች አንዳንዶቹ ዕጣኑንና የሽቱውን ቅባት ያዘጋጁ ነበር። 31 የቆሬያዊውም የሰሎም በኵር ሌዋዊው ማቲትያ ለታላቁ ሊቀ ካህናት በምጣድ በሚጋገረው ነገር ላይ ሹም ነበረ። 32 በየሰንበቱም ያዘጋጁ ዘንድ ቀዓታዊው በንያስና ወንድሞቻቸው በገጹ ኅብስት ላይ ሹሞች ነበሩ። 33 ከሌዋውያንም ወገን የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች የነበሩ መዘምራን በየሰሞናቸው አገልጋዮችና ሹሞች ነበሩ፤ ሥራቸውም ሌሊትና ቀን ነበረ። 34 እነዚህ ከሌዋውያን የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች በየትውልዳቸው አለቆች ነበሩ። እነዚህም በኢየሩሳሌም ይቀመጡ ነበር። 35 የሚስቱ ስም መዓካ የነበረው የገባዖን አባት ይዒኤል በገባዖን ይቀመጥ ነበረ። 36 የበኵር ልጁም ስም ዓብዶን፥ሁለተኛው ሲር፥ ሦስተኛው ቂስ፥ አራተኛው በኣል፥ አምስተኛው ኔር፥ ስድስተኛውም ናዳብ፤ 37 ሰባተኛው ግዱር፥ ወንድሙ ዘካርያስም፥ ሜቅሎትም። 38 ሜቅሎትም ሳምአን ወለደ፤ እነርሱም ደግሞ ከወንድሞቻቸው ጋር በኢየሩሳሌም በወንድሞቻቸው መካከል ይቀመጡ ነበር። 39 ኔርም ቂስን ወለደ፤ ቂስም ሳኦልን ወለደ፤ ሳኦልም ዮናታንን፥ ሜልኪሳን፥ አሚናዳብን፥ አስበኣልን ወለደ። 40 የዮናታንም ልጅ መሪበኣል ነበረ፤ መሪበኣልም ሚካን ወለደ። 41 የሚካም ልጆች ፒቶን፥ ሜሌክ፥ ታራ፥ አካዝ ነበሩ፤ 42 አካዝም ኢያዳዕን ወለደ፤ ኢያዳዕም ጋሌሜትን፥ ጋዝሞትን፥ ዘምሪን ወለደ፤ ዘምሪም ማሳዕን ወለደ። 43 ማሳዕም በዓናን ወለደ፥ ልጁ ረፋያ ነበረ፥ ልጁ ኤልዓሣ፥ ልጁ ኤሴል፤ 44 ለኤሴልም ስድስት ልጆች ነበሩት፤ ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ዓዝሪቃም፥ ቦኬርዩ፥ እስማኤል፥ ሰዓርያ፥ አብድዩ፥ ሐናን፤ እነዚህ የኤሴል ልጆች ነበሩ። |