1 ዜና መዋዕል 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ትውልድ 1 የይሁዳ ልጆች ፋሬስ፥ ኤስሮም ከርሚ፥ ሆርና ሱባል ናቸው። 2 የሱባልም ልጅ ራያ ኢኤትን ወለደ፤ ኢኤትም አሑማይንና ላሃድን ወለደ። እነዚህ የሰራአውያን ትውልዶች ናቸው። 3 እነዚህም የኤጣም ልጆች ናቸው፤ ኢይዝራኤል፥ ይሰማ፥ ኤጋቢስ፥ እኅታቸውም ኤሴልፎን። 4 የጌዶርም አባት ፋኑኤል፥ የአሶን አባት አዜር፤ እነዚህ የቤተ ልሔም አባት የኤፍራታ የበኵሩ የሆር ልጆች ናቸው። 5 ለቴቁሄም አባት ለአስሑር ሔላና ነዓራ የተባሉ ሁለት ሚስቶች ነበሩት። 6 ነዓራም አሑዛምን፥ ኦፌርን፥ ቴማንንና አስትራን ወለደችለት። እነዚህ የነዓራ ልጆች ናቸው። 7 የሔላም ልጆች ሴሬት፥ ይጽሐርና ኢትናን ናቸው። 8 ቆስ፥ ኢኖብን፥ ሲባባን፥ የሃሩምንም ልጅ የሬካብን ወንድም ወገኖች ወለደ። 9 ያግቤጽም ከወንድሞቹ ይልቅ የተከበረ ነበረ፤ እናቱም፦ በጣር ወልጄዋለሁና ብላ ስሙን፦ ያግቤጽ ብላ ጠራችው። 10 ያግቤጽም፥ “እባክህ፥ መባረክን ባርከኝ፥ ሀገሬንም አስፋው፤ እጅህም ከእኔ ጋር ትሁን፤ እንዳያሳዝነኝም ምልክት አድርግልኝ” ብሎ የእስራኤልን አምላክ ጠራ፤ እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው። 11 የሱሃም ወንድም ካሌብ የኤስቶንን አባት ማኪርን ወለደ። 12 ኤስቶንም ቤቶራፋንና ፋሲሓን፥ የቄኔዛዊው የኤሴሎምን ወንድም የነዓስ ከተማ አባት ታሒናን ወለደ፤ እነዚህ የራፋ ሰዎች ናቸው። 13 የቄኔዝም ልጆች ጎቶንያልና ሠራኢያ ነበሩ። የጎቶንያልም ልጅ አታት ነበረ። 14 መናቲም ጎፍራን ወለደ። ሠራኢያም የጌራሲምን አባት ኢዮአብን ወለደ፤ እነርሱም ጠራቢዎች ነበሩ። 15 የዮፎኒም ልጅ የካሌብ ልጆች ዔሩ፥ ኤላ፥ ነዓም ነበሩ። የኤላም ልጅ ቄኔዝ ነበረ። 16 የኢያልኤል ልጆች ዜፍ፥ ዚፋ፥ ቲርያ፥ አሣርኤል ነበሩ። 17 የኤዜራስም ልጆች፤ ኢያቴር፥ ሞራድ፥ ጋፌር፥ ኢያሎን ነበሩ፤ ኢያቴርም ማሮንን፥ ሰማዒን፥ የኢስቲሞንን አባት ይስባኤልን ወለደ። 18 ሚስቱ አይሂዳም የጌዶርን አባት ያሬድን፥ የሦኮንም አባት ሔቤርን፥ የዛኖዋንም አባት ይቁቲኤልን ወለደች። እነዚህ ሞሬድ ያገባት የፈርዖን ልጅ የቢትያ ልጆች ናቸው። 19 የሆድያ ሚስት የነሐም እኅት ልጆች የገርሜው የቅዔላ አባትና ማዕካታዊው ኤሲትሞዓ ነበሩ። 20 የሴሞንም ልጆች አምኖን፥ የአናን ልጆች ሬኖንና ቲሎን ነበሩ፤ የይስቴም ልጆች ዘካትና የዘካት ልጆች ነበሩ። 21 የይሁዳም ልጅ የሴሎም ልጆች የሌካ አባት ዔር፥ የመሪሳ አባት ለዓዳ፥ ከአስቤዓ ቤት የሚሆኑ ጥሩ በፍታ የሚሠሩ ወገኖች፥ 22 ኢዮአቄም፥ የካዚባ ሰዎች፥ ኢዮአስ፥ በሞዓብ አድሮ ስማቸውን፥ አብዶራንና ተቂኤም ብሎ የመለሰ ሣራፍ ነበሩ። 23 እነዚህ በነጣዔምና በጋዲራ ከንጉሡ ጋር የሚቀመጡ ሸክላ ሠራተኞች ነበሩ። እነርሱም በመንግሥቱ ጸንተው በዚያ ይኖሩ ነበር። 24 የስምዖንም ልጆች፤ ነሙኤል፥ ያሚን፥ ያሪብ፥ ዛራ፥ ሳኡል፤ 25 ልጁ ሳሌም፥ ልጁ መብሳም፥ ልጁ ማስማዕ። 26 የማስማዕም ልጆች፤ ልጁ ሃሙኤል፥ ልጁ ሳባድ፥ ልጁ ዝኩር፥ ልጁ ሰሜኢ። 27 ለሰሜኢም ዐሥራ ስድስት ወንዶችና ስድስት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ለወንድሞቹ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፥ ወገናቸውም ሁሉ እንደ ይሁዳ ልጆች አልተባዙም። 28 በቤርሳቤህም፥ በሰምዓም፥ በሞላዳ፥ በሐጸርሱዓል፥ 29 በቤልሃ፥ በዔጼም፥ በቶላድ፤ 30 በቤቱኤል፥ በሔርማ፥ በሤቄላቅ፤ 31 በቤትማርካቦት፥ በሐጸርሱሲም፥ በቤትቢሪ፥ በሰዓራይም ይቀመጡ ነበር። እስከ ዳዊትም መንግሥት ድረስ ከተሞቻቸው እነዚህ ነበሩ። 32 መንደሮቻቸውም ኤጣም፥ ዓይን፥ ሬሞን፥ ቶኪን፥ ዓሻን፥ አምስቱ ከተሞች፤ 33 መንደሮቻቸውም ሁሉ እስከ በኣል ድረስ በእነዚህ ከተሞች ዙሪያ ነበሩ። መቀመጫቸውና ድርሻቸውም ይህ ነበረ። 34 መሶባብ፥ የምሌክ፥ የአሚስያስ ልጅ ኢዮስያ፤ 35 ኢዮኤል፥ የዮስብያ ልጅ፥ የሠራያ ልጅ የአሣኤል ልጅ ኢዩ፤ 36 ኤልዮዔናይ፥ ያዕቀባ፥ የሰሐያ፥ ዓሣያ፥ ዓዲዔል፥ ይስማኤል፥ በናያስ፤ 37 የሳፋኤ ልጅ ዙዛ፥ የአሎን ልጅ የይዳያ ልጅ የሰማሪ ልጅ የሰማያ ልጅ፤ 38 እነዚህ በስማቸው የተጠሩ በወገኖቻቸው ላይ አለቆች ነበሩ፤ የአባቶቻቸውም ቤቶች በዝተው ነበር። 39 ለመንጎቻቸው መሰማርያ ይሹ ዘንድ ወደ ጌራራ እስኪደርሱ ድረስ ወደ ጋይ ምሥራቅ ሄዱ። 40 ብዙና እጅግ ያማረ መሰማርያም አገኙ፤ ምድሪቱም በፊታቸው ሰፊና ጸጥተኛ ሰላም ያላትም ነበረች፤ በቀድሞም ጊዜ በዚያ ተቀምጠው የነበሩ ከካም ወገን ነበሩ። 41 በስማቸው የተጻፉ እነዚህም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን መጥተው ድንኳኖቻቸውንና በዚያ የተገኙትን ምዑናውያንን መቱ፥ እስከ ዛሬም ድረስ ፈጽመው አጠፉአቸው፤ በዚያም ለመንጎቻቸው መሰማሪያ ነበርና በስፍራቸው ተቀመጡ። 42 ከስምዖንም ልጆች አምስት መቶ ሰዎች ወደ ሴይር ተራራ ሄዱ፤ አለቆቻቸውም የይሰዔ ልጆች ፥ ፈላጥያ፥ ነዓርያ፥ ረፋያ፥ ዑዝኤል ነበሩ። 43 ያመለጡትንም የአማሌቃውያንን ቅሬታ መቱ፥ በዚያም እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጠዋል። |