1 ዜና መዋዕል 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ዳዊትም በሸመገለ ጊዜ፥ ዕድሜንም በጠገበ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን በእርሱ ፋንታ በእስራኤል ላይ አነገሠው። 2 የእስራኤልንም አለቆች ሁሉ፥ ካህናቱንም፥ ሌዋውያኑንም ሰበሰበ። 3 ሌዋውያንም ከሠላሳ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ ተቈጠሩ፤ ቍጥራቸውም በእያንዳንዱ ነፍስ ወከፍ ሲቈጠሩ ሠላሳ ስምንት ሺህ ነበረ። 4 ከእነዚህም ውስጥ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ የሚያሠሩት ሃያ አራት ሺህ ነበሩ፤ ስድስቱ ሺህም ጻፎችና ፈራጆች ነበሩ። 5 አራቱ ሺህም በረኞች ነበሩ፤ አራቱ ሺህም ለምስጋና በተሠሩት በዜማ ዕቃዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። 6 ዳዊትም እንደ ሌዊ ልጆች እንደ ጌድሶንና እንደ ቀዓት እንደ ሜራሪም በየሰሞናቸው መደባቸው። 7 ከጌድሶናውያን ለአዳንና ሰሜኢ ነበሩ። 8 የለአዳን ልጆች አለቃው አድሔኤል፥ ዜቶም፥ ዮሔል ሦስት ነበሩ። 9 የሰሜኢ ልጆች ሰሎሚት፥ ሐዝኤል፥ ሐራን ሦስት ነበሩ። እነዚህ የለያአዳን አባቶች ቤቶች አለቆች ነበሩ። 10 የሰሜኢ ልጆች ኤኢት፥ ዚዛ፥ ኢያአስ፥ በሪዓ ነበሩ። እነዚህ አራቱ የሰሜኢ ልጆች ነበሩ። 11 አለቃው ኤኢት ነበረ፤ ሁለተኛው ዚዛ ነበረ፤ ኢያአስና በሪዓ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህ እንደ አንድ አባት ቤት ሆነው ተቈጠሩ። 12 የቀዓት ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፦ ኬብሮን፥ ዑዝኤል አራት ነበሩ። 13 የእንበረም ልጆች አሮንና ሙሴ ነበሩ፤ አሮንም ለቅድስተ ቅዱሳን የተቀደሰ ይሆን ዘንድ ተመረጠ፤ እርሱና ልጆቹ ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ፊት ያጥኑና ያገለግሉ ነበር፤ በስሙም ለዘለዓለም ይባርኩ ነበር። 14 የእግዚአብሔርም ሰው ሙሴና ልጆቹ በሌዊ ነገድ ተቈጠሩ። 15 የሙሴ ልጆችም ጌርሳምና አልዓዛር ነበሩ። 16 የጌርሳም ልጆች አለቃ ሱባኤል ነበረ። 17 የአልዓዛርም ልጆች አለቃ ረዓብያ ነበረ፤ አልዓዛርም ሌሎች ልጆች አልነበሩትም፤ የረዓብያ ልጆች እጅግ ብዙ ነበሩ። 18 የይስዓር ልጆች አለቃው ሰሎሚት ነበረ። 19 የኬብሮን ልጆች አለቃው ኢያኤርያ፥ ሁለተኛው አማርያ፥ ሦስተኛው ኢያዝሔል፥ አራተኛው ኢያቄምያስ ነበሩ። 20 የዑዝኤል ልጆች አለቃው ሚካ፥ ሁለተኛው ይስያ ነበሩ። 21 የሜራሪ ልጆች ሞዓሊና ሐሙሲ ነበሩ። የሞዓሊ ልጆች አልዓዛርና ቂስ ነበሩ። 22 አልዓዛርም ሴቶች ልጆች ብቻ እንጂ ወንዶች ልጆች ሳይወልድ ሞተ፤ ወንድሞቻቸውም የቂስ ልጆች አገቡአቸው። 23 የሐሙሲ ልጆች፤ ሞዓሊ፥ አዴር፥ ኢያሪሞት ሦስት ነበሩ። 24 የእግዚአብሔርን ቤት አገልግሎት በሠሩ ከሃያ አምስት ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ በነበሩ በእያንዳንዳቸው በስማቸው በተቈጠሩት ላይ የአባቶች ቤት አለቆች የሆኑት በየአባቶቻቸው ቤት የሌዊ ልጆች እነዚህ ነበሩ። 25 ዳዊትም እንዲህ አለ፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዕረፍት ሰጥቶአል፤ በኢየሩሳሌምም ለዘለዓለም ይቀመጣል። 26 ሌዋውያንም ከእንግዲህ ወዲህ ማደሪያውንና የማገልገያ ዕቃውን ሁሉ አይሽከሙም።” 27 በመጨረሻውም በዳዊት ትእዛዝ ከሃያ አምስት ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት የሌዊ ልጆች ተቈጠሩ። 28 የእግዚአብሔርንም ቤት በየአደባባዩና በየመጋረጃው ውስጥ ለማገልገል፥ ቅዱሱንም ዕቃ ሁሉ ለማንጻት፥ የእግዚአብሔርንም ቤት አገልግሎት ለመሥራት ከአሮን ልጆች እጅ በታች ሹሞአቸው ነበር። 29 ደግሞም ገጸ ኅብስት፥ ስስ ቂጣም ቢሆን፥ በምጣድም ቢጋገር፥ ቢለወስም ለእህል ቍርባን በሆነው በመልካሙ ዱቄት በመስፈሪያና በልክ ሁሉ ያገለግሉ ዘንድ ሹሞአቸው ነበር። 30 በየጥዋቱና በየማታው ቆመው እግዚአብሔርን ለማመስገንና ለማክበር፥ 31 በየሰንበታቱም፥ በየመባቻዎቹም፥ በየበዓላቱም እንደ ሥርዐቱ ቍጥር በእግዚአብሔር ፊት ዘወትር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ ለማቅረብ፥ 32 ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የምስክሩን ድንኳን ሥርዐት፥ የወንድሞቻቸውን የአሮንን ልጆች ሥርዐት ለመጠበቅ ሹሞአቸው ነበር። |