1 ዜና መዋዕል 22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ቤተ መቅደስን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት 1 ዳዊትም፥ “ይህ የአምላኬ የእግዚአብሔር ቤት ነው፤ ይህም ለእስራኤል ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ ነው” አለ። 2 ዳዊትም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ይሰበስቡ ዘንድ አዘዘ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ለመሥራት የሚወቀሩትን ድንጋዮች ይወቅሩ ዘንድ ጠራቢዎችን አኖረ። 3 ዳዊትም ለበሮቹ ሳንቃ ለሚሆኑ ለምስማርና ለመጠረቂያ ብዙ ብረት፥ ከብዛቱም የተነሣ የማይመዘን ናስ አዘጋጀ። 4 ሲዶናውያንና የጢሮስ ሰዎችም ብዙ የዝግባ እንጨት ለዳዊት ያመጡ ነበርና ቍጥር የሌላቸውን የዝግባ እንጨቶች አዘጋጀ። 5 ዳዊትም፥ “ልጄ ሰሎሞን ታናሽና ለጋ ብላቴና ነው፤ ለእግዚአብሔርም የሚሠራው ቤት እጅግ ማለፊያና በሀገሩ ሁሉ ስሙና ክብሩ እንዲጠራ ይሆን ዘንድ ይገባል፤ ስለዚህ አዘጋጅለታለሁ” አለ። ዳዊትም ሳይሞት አስቀድሞ ብዙ አዘጋጀ። 6 ልጁንም ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ አዘዘው። 7 ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፥ “ልጄ ሆይ፥ እኔ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራ ዘንድ በልቤ አስቤ ነበር። 8 ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ እጅግ ብዙ ደም አፍስሰሃል፤ ታላቅም ሰልፍ አድርገሃል፤ በፊቴም በምድር ላይ ብዙ ደም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም። 9 እነሆ፥ ልጅ ይወለድልሃል፤ የዕረፍት ሰውም ይሆናል፤ በዙሪያውም ካሉ ከጠላቶቹ ሁሉ አሳርፈዋለሁ፤ ስሙ ሰሎሞን ይባላልና፥ በዘመኑም ሰላምንና ጸጥታን ለእስራኤል እሰጣለሁ። 10 እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፤ ልጅም ይሆነኛል፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ የመንግሥቱንም ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም አጸናለሁ። 11 አሁንም ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም እንደ ተናገረው ያከናውንልህ፤ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ። 12 ብቻ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ሕግ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ፤ መንግሥትህንም በእስራኤል ላይ ያጽና። 13 እግዚአብሔር ስለ እስራኤል ሙሴን ያዘዘውን ሥርዐትና ፍርድ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ ብትጠነቀቅ በዚያን ጊዜ ይከናወንልሃል፤ አይዞህ፥ በርታ፤ አትፍራ፤ አትደንግጥም። 14 አሁንም፥ እነሆ፥ በድህነቴ ለእግዚአብሔር ቤት መቶ ሺህ መክሊት ወርቅና አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፥ ሚዛንም የሌላቸው ብዙ ናስና ብረት አዘጋጅቻለሁ፤ ደግሞም የማይቈጠር ብዙ የዝግባ እንጨትና ድንጋዮች አዘጋጅቻለሁ፤ አንተም ልጄ ከዚያ በላይ ጨምር። 15 አንተም ብዙ ሠራተኞችን፥ ድንጋይና እንጨት ወቃሪዎችንና ጠራቢዎችን፥ ሥራውንም ሁሉ ለማድረግ ጠቢባን ሰዎችን አብዝተህ ጨምር። 16 ቍጥር በሌለው በወርቅና ብር፥ በናስና ብረት ተነሥተህ ሥራ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን።” 17 ዳዊትም ደግሞ ልጁን ሰሎሞንን ይቀበሉትና ያግዙት ዘንድ የእስራኤልን አለቆች ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ 18 “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይደለምን? በምድርም የሚቀመጡትን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ምድርም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ፊት ተገዝታለችና በዙሪያችሁ ከአሉ ጠላቶቻችሁም ሁሉ ዕረፍትን ሰጥቶአችኋል። 19 አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈልጉ ዘንድ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ስጡ፤ ለእግዚአብሔርም ስም ወደሚሠራው ቤት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦትና የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ታመጡ ዘንድ ተነሥታችሁ የአምላክን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ።” |