1 ዜና መዋዕል 20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዳዊት አራቦትን እንደ ያዘ ( 2ሳሙ. 12፥26-31 ) 1 እንዲህም ሆነ፤ በዓመት መጨረሻ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ ኢዮአብ የሠራዊቱን ኀይል አወጣ፤ የአሞንንም ልጆች ሀገር አጠፋ፤ መጥቶም አራቦትን ከበበ። ዳዊትም በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ነበር። ኢዮአብም አራቦትን መትቶ አፈረሳት። 2 ዳዊትም የንጉሣቸውን የሞልኮልን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ሆኖ ተገኘ፤ ክቡር ዕንቍም ነበረበት፤ በዳዊትም ራስ ላይ አስቀመጡት፤ ከከተማዪቱም እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰደ። 3 በውስጥዋም የነበሩትን ሕዝብ አውጥተው በመጋዝ ተረተሩአቸው፤ በመጥረቢያም ቈራረጡአቸው። ዳዊትም በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 4 ከዚህም በኋላ በጋዜር ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጦርነት እንደ ገና ሆነ፤ ያንጊዜም ኡሳታዊው ሴቦቃይ ከኀያላን ወገን የነበረውን ሲፋይን ገድሎ ጣለው። 5 ደግሞም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ነበረ፤ የያዔርም ልጅ ኤልያናን የጌት ሰው የጎልያድን ወንድም ለሕሜን ገደለ። የጦሩ የቦም እንደ ሸማኔ መጠቅለያ ሆኖ ተገኘ። 6 ደግሞ በጌት ላይ ሰልፍ ሆነ ፤ በዚያም በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስት ጣቶች በጠቅላላው ሃያ አራት ጣቶች ያሉት አንድ ረዥም ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከኀያላን የተወለደ ነበረ። 7 እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ዮናታን ገደለው። 8 እነዚህም በጌት ውስጥ ከኀያላን የተወለዱ ነበሩ፤ እነርሱም አራት ኀያላን ነበሩ፤ በዳዊትም እጅ በአገልጋዮቹም እጅ ወደቁ። |