1 ዜና መዋዕል 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዳዊት በኢየሩሳሌም የፈጸማቸው ተግባራት ( 2ሳሙ. 5፥11-16 ) 1 የጢሮስም ንጉሥ ኪራም ቤት ይሠሩለት ዘንድ መልእክተኞችን፥ የዝግባ እንጨትንም፥ ጠራቢዎችንም፥ አናጢዎችንም ወደ ዳዊት ላከ። 2 ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል፥ መንግሥቱ እጅግ ከፍ ብሎአልና እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን እንዳዘጋጀው ዳዊት ዐወቀ። 3 ዳዊትም በኢየሩሳሌም ሌሎች ሚስቶችን ጨምሮ አገባ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት። 4 በኢየሩሳሌምም የተወለዱለት የልጆቹ ስም ይህ ነው፤ ሳማ፥ ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፤ 5 በዓር፥ ኤሊሳዒ፥ ኤሌፋላት፤ 6 ናጌት፥ ናፋት፥ ያፍያ፥ 7 ኤሊሳማ፥ በለዓዳ፥ ኤሊፋላት። ዳዊት በፍልስጥኤማውያን ላይ የተቀዳጀው ድል ( 2ሳሙ. 5፥17-25 ) 8 ፍልስጥኤማውያንም ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደ ተቀባ ሰሙ፤ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ሊጋጠማቸው ወጣ። 9 ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በኀያላን ሸለቆ ተሰበሰቡ። 10 ዳዊትም፥ “ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፥ “በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ” አለው። 11 ዳዊትም ወደ በኣልፐራሲን ወጣ፤ በዚያም ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን መታቸው። ዳዊትም፥ “ውኃ እንዲያጠፋ እግዚአብሔር ጠላቶቼን በእጄ አጠፋቸው” አለ። ስለዚህም የዚያን ስፍራ ስም በኣልፐራሲን ብለው ጠሩት። 12 አማልክቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፤ ዳዊትም፥ “በእሳት አቃጥሉአቸው” ብሎ አዘዘ። 13 ፍልስጥኤማውያንም ደግሞ በኀያላን ሸለቆ ተሰበሰቡ። 14 ዳዊትም እንደ ገና እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም፥ “አትውጣ፥ በኋላቸውም አትከተላቸው፤ ነገር ግን ከኋላቸው ዙረህ ቅረባቸው። 15 በሾላውም ዛፍ ራስ ውስጥ የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ሊመታ እግዚአብሔር በፊትህ ይወጣልና በዚያን ጊዜ ወደ ሰልፍ ውጣ” አለው። 16 ዳዊትም አምላኩ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖንም ጀምሮ እስከ ጌዝር ድረስ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መታ። 17 የዳዊትም ዝና በየሀገሩ ሁሉ ወጣ፤ መፈራቱንም እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ አደረገ። |