1 ዜና መዋዕል 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መወሰድዋ ( 2ሳሙ. 6፥1-11 ) 1 ዳዊትም ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች፥ ከአለቆቹም ሁሉ ጋር ተማከረ። 2 ዳዊትም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ፥ “መልካም መስሎ የታያችሁ እንደ ሆነ፥ አምላካችን እግዚአብሔርም ፈቅዶ እንደ ሆነ፥ በእስራኤል ሀገር ሁሉ ለቀሩት ወንድሞቻችን በከተሞቻቸውና በመሰማሪያዎቻቸው ለሚቀመጡ ካህናትና ሌዋውያን ወደ እኛ ይሰበሰቡ ዘንድ እንላክ። 3 ከሳኦልም ዘመን ጀምሮ አልፈለጓትምና የአምላካችን የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኛ እንመልሳት” አላቸው። 4 ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዐይን ዘንድ ቅን ነበረና የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ፥ “እንዲሁ እናደርጋለን” አሉ። 5 የእግዚአብሔርንም ታቦት ከቂርያትይዓሪም ያመጡ ዘንድ ዳዊት እስራኤልን ሁሉ ከግብፅ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ኤማት መግቢያ ድረስ ሰበሰበ። 6 ዳዊትም፥ እስራኤልም ሁሉ በኪሩቤል ላይ የተቀመጠውን፥ ስሙም በእርስዋ የተጠራባትን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያወጡ ዘንድ በይሁዳ ወዳለችው ቂርያትይዓሪም ሄዱ። 7 የእግዚአብሔርንም ታቦት ከአሚናዳብ ቤት በተገኘ በአዲስ ሰረገላ ላይ አኖሩአት። ዖዛና ወንድሞቹም ሰረገላውን ይነዱ ነበር። 8 ዳዊትና እስራኤል ሁሉ ከመዘምራን ጋር በበገና፥ በመሰንቆና በከበሮ፥ በጸናጽልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኀይላቸው ይዘምሩ ነበር። 9 ወደ አውድማ ዳርም በደረሱ ጊዜ ላሞቹ ሰረገላውን ሲስቡ የእግዚአብሔር ታቦት ዘንበል ብላለችና ታቦቷን ሊይዝ ዖዛ እጁን ዘረጋ። 10 እግዚአብሔርም በዖዛ ላይ ተቈጣ። እጁንም ወደ እግዚአብሔር ታቦት ስለ ዘረጋ ቀሠፈው፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ። 11 እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ሰበረው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያን ስፍራ ስም “የዖዛ ስብራት” ብሎ ጠራው። 12 በዚያም ቀን ዳዊት፥ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት አመጣለሁ?” ብሎ እግዚአብሔርን ፈራ። 13 ዳዊትም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ጌት ሰው ወደ አቢዳራ ቤት አሳለፋት እንጂ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ አላመጣትም። 14 የእግዚአብሔርም ታቦት በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት ውስጥ ሦስት ወር ተቀመጠች፤ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤተ ሰቡን ሁሉ ባረከ። |