1 ዜና መዋዕል 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዳዊት በይሁዳና በእስራኤል ላይ እንደ ነገሠ ( 2ሳሙ. 5፥1-10 ) 1 እስራኤልም ሁሉ በኬብሮን ወደ ዳዊት ተሰብስበው እንዲህ አሉት፥ “እነሆ፥ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቍራጭ ነን፤ 2 አስቀድሞ ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፤ አምላክህ እግዚአብሔርም፦ ሕዝቤን እስራኤልን አንተ ትጠብቃለህ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆናለህ” አለህ። 3 የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሥ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ በሳሙኤልም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል በእስራኤል ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊትን ቀቡት። 4 ዳዊትና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ኢያቡስ ወደምትባል ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፤ በሀገሩም የተቀመጡ ኢያቡሳውያን በዚያ ነበሩ። 5 በኢያቡስም የተቀመጡ ዳዊትን፥ “ወደዚህ አትገባም” አሉት፤ ዳዊት ግን አንባዪቱን ጽዮንን ያዘ፤ እርስዋም የዳዊት ከተማ ናት። 6 ዳዊትም ኢያቡሳውያንን አስቀድሞ የሚመታ ሰው አለቃና መኰንን ይሆናል አለ። የሶርህያም ልጅ ኢዮአብ አስቀድሞ ወጣና ወጋቸው፥ አለቃም ሆነ። 7 ዳዊትም በአንባዪቱ ውስጥ ተቀመጠ፤ ስለዚህም “የዳዊት ከተማ” ብለው ጠሩአት። 8 ዳዊትም የከተማዋን ዙሪያ ቀጸረ፤ ተዋግቶም እጅ አደረጋት። 9 ዳዊትም ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና እየበረታ ሄደ። የዳዊት ኀያላን ( 2ሳሙ. 23፥8-39 ) 10 ለዳዊትም የነበሩት ኀያላን አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ስለ እስራኤል እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ያነግሡት ዘንድ ከእስራኤል ሁሉ ጋር በመንግሥቱ አጸኑት። 11 የዳዊትም ኀያላን ቍጥር ይህ ነበረ፤ የሠላሳው አለቃ የአኪማን ልጅ ኢያቡስቴ ነበረ፤ እርሱ ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰው በአንድ ጊዜ ገደለ። 12 ከእርሱም በኋላ በሦስቱ ኀያላን መካከል የነበረ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ አልዓዛር ነበረ። 13 እርሱ ከዳዊት ጋር በፋሶደሚን ነበረ፥ በዚያም ገብስ በሞላበት እርሻ ውስጥ ፍልስጥኤማውያን ለሰልፍ ተሰብስበው ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። 14 በእርሻውም መካከል ቆመው ጠበቁት፥ ያችንም ቦታ አዳናት፤ ፍልስጥኤማውያንንም ገደላቸው፤ እግዚአብሔርም በታላቅ ማዳን አዳናቸው። 15 ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓለቱ ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በኀያላን ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። 16 በዚያም ጊዜ ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በቤተ ልሔም ነበረ። 17 ዳዊትም፥ “በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ማን ይሰጠኛል?” ብሎ ተመኘ። 18 እነዚህ ሦስቱ ኀያላን የፍልስጥኤማውያንን ሰፈር ሰንጥቀው ሄዱ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፤ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፥ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፍስሶ፦ 19 “ይህን አደርግ ዘንድ አምላኬ ሆይ፥ ለእኔ አይገባኝም፤ ሰውነታቸውንም ለሞት አሳልፈው አምጥተውታልና የእነዚህን ሰዎች ደም እጠጣለሁን?” አለ። ስለዚህም ዳዊት ይጠጣው ዘንድ አልወደደም። ሦስቱም ኀያላን ያደረጉት ይህ ነው። 20 የኢዮአብም ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበረ፤ ሰይፉንም በሦስት መቶ ላይ አንሥቶ በአንድ ጊዜ ገደላቸው፤ በሦስቱም መካከል ስሙ የተጠራ ነበረ። 21 በሁለተኛውም ተራ በሆኑት በሦስቱ መካከል የከበረ ነበረ፥ አለቃቸውም ሆነ፤ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም። 22 በቀበሳኤል የነበረው፥ ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ እንደ አንበሳ ኀያላን የነበሩትን ሁለት የሞዓብ ሰዎች ገደለ፤ በአመዳይም ወራት ወርዶ በጕድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ። 23 ቁመቱም አምስት ክንድ የነበረውን ረጅሙን ግብፃዊውን ሰው ገደለ፤ በግብፃዊውም እጅ የሸማኔ መጠቅለያ የመሰለ ጦር ነበረ፤ እርሱ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፥ ከግብፃዊውም እጅ ጦሩን ቀምቶ በገዛ ጦሩ ገደለው። 24 የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም በሦስቱ ኀያላን መካከል የተጠራ ነበረ። 25 እነሆ፥ ከሠላሳው ይልቅ የከበረ ነበረ፤ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በናያስን በሀገሩ ላይ ሾመው። 26 ደግሞም በጭፍሮቹ ዘንድ የነበሩት ኀያላን እነዚህ ናቸው፤ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ የቤተ ልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፤ 27 ሃሮራዊው ሳሞት፥ ፈሎናዊው ኬሌስ፤ 28 የቴቁሔ ሰው የአቂስ ልጅ ኦራ፥ ዓናቶታዊው አቤዔዜር፤ 29 ኩሳታዊው ሰቦካይ፥ የአሆሂው ዔላይ፤ 30 ነጦፋዊው ሜሐሪ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌድ፤ 31 ከብንያም ወገን ከጊብዓ የሪባይ ልጅ ኢታይ፥ ፈርኖታዊው ባንያስ፤ 32 የገዓዝ ወንዝ ሰው ኡሪ፥ ገራባታዊው አብኤል፥ 33 ባሮማዊው ዓዝሞት፥ ሰዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፤ 34 የጊዞንያዊው የኤሳም ልጅ፥ የአሩራዊው የሶላ ልጅ ዮናታን፤ 35 የአሮራዊው የሳኮር ልጅ አህያም፥ የኤር ልጅ ኤሊፋል፤ 36 መከራታዊው ኦፌር፥ ፍሎናዊው አኪያ፤ 37 ቀርሜሎሳዊው ሴራይ፥ የኤዝባይ ልጅ ናራይ፤ 38 የናታንም ወንድም ኢዩኤል፥ የሐገሪ ልጅ ሚብሐር፤ 39 አሞናዊው ሴሌቅ፥ የሦርህያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮታዊው ናኮር፤ 40 ይትራዊው ዔራ፥ ይትራዊው ጋሬብ፤ 41 ኬጢያዊው ዑርያስ፥ የአሕላይ ልጅ ዘባት፤ 42 የሮቤላዊው የሲዛ ልጅ ዓዲና፥ እርሱ የሮቤላውያን አለቃ ነበረ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሰዎች ነበሩ፤ 43 የሞካ ልጅ ሐናን፥ ሚትናዊው ኢዮሣፍጥ፤ 44 አስታሮታዊው ዖዝያ፥ የአሮዔራዊው የኮታም ልጆች ሳማና ይዒኤል፤ 45 የሳምሪ ልጅ ይዳኤል፥ ወንድሙም ቲዳዊው ዮዛሔ፥ 46 መዓዊው ኤሊኤል፤ ኢያርባኢ፥ ልጁ ዮሳኢ፥ ኤልነዓምና ሞዓባዊው ይትማ፤ 47 ኤሊኤል፥ ዖቤድ፥ ምሶባዊው ኢያስኤል። |