1 ዜና መዋዕል 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ንጉሥ ሳኦል እንደ ሞተ ( 1ሳሙ. 31፥1-13 ) 1 በዚያም ወራት ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጌላቡሄ ተራራ ላይ ወደቁ። 2 ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ። 3 ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ። ቀስተኞችም አግኝተው ወጉት፤ ከቀስቶችም ኀይል የተነሣ ተጨነቀ። 4 ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፥ “እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይዘብቱብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ” አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ። 5 ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ። 6 ሳኦልና ሦስቱም ልጆቹ የቤቱም ሰዎች ሁሉ በዚያች ቀን በአንድ ላይ ሞቱ። 7 በሸለቆውም የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እስራኤል እንደ ሸሹ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው። 8 በነጋውም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልንና ልጆቹን በጌላቡሄ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው። 9 ሳኦልንም ገፈፉት፥ ራሱንም ቈርጠው መሣሪያውንም አንሥተው ለጣዖቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራች ይወስዱ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን ሀገር ዙሪያ ሰደዱ። 10 መሣሪያውንም በአምላኮቻቸው ቤት ውስጥ አኖሩ፤ ራሱንም በዳጎን ቤት ውስጥ አኖሩት፤ 11 የገለዓድም ሰዎች ሁሉ ፍልስጥኤማውያን በሳኦልና በእስራኤል ላይ ያደረጉትን ሁሉ ሰሙ። 12 ጽኑዓን ሰዎች ሁሉ ከገለዐድ ተነሥተው የሳኦልን ሬሳ የልጆቹንም ሬሳዎች ወሰዱ፥ ወደ ኢያቢስም አመጡአቸው፤ በኢያቢስም ካለው ከትልቁ ዛፍ በታች አጥንቶቻቸውን ቀበሩ፥ ሰባት ቀንም ጾሙ። 13 እንዲሁ ሳኦል በእግዚአብሔር ላይ ስላደረገው ኀጢአት፥ እግዚአብሔርም እንዳዘዘው የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቀ ሞተ። ደግሞም መናፍስት ጠሪን ጠየቀ። 14 ነቢዩ ሳሙኤልም መለሰለት፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ ዘንድ አልሰማውም፥ ስለዚህ ገደለው፤ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አሳለፈው። |