መዝሙር 70 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 70 70፥1-5 ተጓ ምብ – መዝ 40፥13-17 ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር፤ ለመታሰቢያ። 1 አምላክ ሆይ፤ ታድነኝ ዘንድ ዘንበል በል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን። 2 ነፍሴን ለመንጠቅ የሚፈልጉ፣ ይፈሩ፤ ይዋረዱም፤ ጕዳቴንም የሚሹ፣ ተዋርደው በመጡበት ይመለሱ። 3 በእኔ ላይ፣ “ዕሠይ! ዕሠይ!” የሚሉ፣ ተሸማቅቀው ወደ ኋላ ይመለሱ። 4 አንተን የሚፈልጉ ሁሉ ግን፣ ሐሤት ያድርጉ፤ በአንተም ደስም ይበላቸው፤ ማዳንህን የሚወድዱ ሁሉ ሁልጊዜ “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል!” ይበሉ። 5 እኔ ግን ችግረኛና ድኻ ነኝ፤ አምላክ ሆይ፤ ፈጥነህ ድረስልኝ፤ አንተ ረዳቴና፣ ታዳጊዬም ነህና፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አትዘግይ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.