መዝሙር 56 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 56 ለመዘምራን አለቃ፤ “ርግቢቱ ሩቅ ባለው ወርካ ላይ” በተባለው ቅኝት፤ ፍልስጥኤማውያን በጋት በያዙት ጊዜ፤ የዳዊት ሚክታም ። 1 እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰዎች መረገጫ ሆኛለሁና ማረኝ፤ ቀኑንም ሙሉ በውጊያ አስጨንቀውኛል። 2 ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ በላዬ ቆሙ፤ በትዕቢት የሚዋጉኝ ብዙዎች ናቸውና። 3 ፍርሀት በሚይዘኝ ጊዜ፣ መታመኔን በአንተ ላይ አደርጋለሁ። 4 ቃሉን በማመሰግነው አምላክ፣ በእግዚአብሔር ታምኛለሁ፤ አልፈራም፤ ሥጋ ለባሽ ምን ሊያደርገኝ ይችላል? 5 ቀኑን ሙሉ ቃሌን ያጣምሙታል፤ ዘወትርም ሊጐዱኝ ያሤራሉ። 6 ይዶልታሉ፤ ያደባሉ፤ ርምጃዬን ይከታተላሉ፤ ነፍሴንም ለማጥፋት ይሻሉ። 7 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከክፋታቸው የተነሣ እንዳያመልጡ፣ ሕዝቦቹን በቍጣህ ጣላቸው። 8 ሰቈቃዬን መዝግብ፤ እንባዬን በዕቃህ አጠራቅም፤ ሁሉስ በመዝገብህ የተያዘ አይደለምን? 9 ወደ አንተ በተጣራሁ ቀን፣ ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ በዚህም፣ አምላክ ከጐኔ መቆሙን ዐውቃለሁ። 10 ቃሉን በማመሰግነው አምላክ፣ ቃሉን በማመሰግነው በእግዚአብሔር፣ 11 በአምላክ ታምኛለሁ፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል? 12 እግዚአብሔር ሆይ፤ የአንተ ስእለት አለብኝ፤ የማቀርብልህም የምስጋና መሥዋዕት ነው፤ 13 በሕያዋን ብርሃን፣ በእግዚአብሔር ፊት እመላለስ ዘንድ፣ ነፍሴን ከሞት፣ እግሬንም ከመሰናክል አድነሃልና። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.