መዝሙር 47 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 47 ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር። 1 ሕዝቦች ሁላችሁ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፤ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር እልል በሉ። 2 በምድር ሁሉ ላይ ታላቅ የሆነው ንጉሥ፣ ልዑል እግዚአብሔር የሚያስፈራ ነውና። 3 ሕዝቦችን ከእኛ በታች አደረገ፤ መንግሥታትንም ከእግራችን ሥር አስገዛልን። 4 ለሚወድደው ለያዕቆብ ክብር የሆነችውን፣ ርስታችንን እርሱ መረጠልን። ሴላ 5 አምላክ በእልልታ፣ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ። 6 አምላካችንን አወድሱት፤ አወድሱት፤ ንጉሣችንን አወድሱት፤ አወድሱት፤ 7 እግዚአብሔር የምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፤ ምርጥ ዝማሬ አቅርቡለት። 8 እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ ነግሧል፤ እግዚአብሔር በተቀደሰ ዙፋኑ ላይ ተቀምጧል። 9 ከአብርሃም አምላክ ሕዝብ ጋራ፣ የሕዝቦች መኳንንት ተሰበሰቡ፤ የምድር ነገሥታት የእግዚአብሔር ናቸውና፤ እርሱም እጅግ ከፍ ከፍ ያለ ነው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.