መዝሙር 135 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 135 135፥15-20 ተጓ ምብ – መዝ 115፥4-11 1 ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔርን ስም ወድሱ፤ እናንተ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሆይ፤ አመስግኑት፤ 2 በእግዚአብሔር ቤት፣ በአምላካችን ቤት አደባባይ የምትቆሙ አመስግኑት። 3 እግዚአብሔር ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ መልካም ነውና፣ ለስሙ ዘምሩ፤ 4 እግዚአብሔር ያዕቆብን ለራሱ፣ እስራኤልንም ውድ ንብረቱ አድርጎ መርጧልና። 5 እግዚአብሔር ታላቅ እንደ ሆነ፣ ጌታችንም ከአማልክት ሁሉ እንደሚበልጥ ዐውቃለሁና። 6 በሰማይና በምድር፣ በባሕርና በጥልቅ ሁሉ ውስጥ፣ እግዚአብሔር ደስ ያሠኘውን ሁሉ ያደርጋል። 7 እርሱ ደመናትን ከምድር ዳርቻ ያስነሣል፤ መብረቅ ከዝናብ ጋራ እንዲወርድ ያደርጋል፤ ነፋሳትንም ከማከማቻው ያወጣል። 8 በኵር ሆኖ በግብጽ የተወለደውን፣ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ቀሠፈ። 9 ግብጽ ሆይ፤ በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ሁሉ ላይ፣ በመካከልሽ ታምራትንና ድንቅን ሰደደ። 10 ብዙ ሕዝቦችን መታ፤ ኀያላን ነገሥታትንም ገደለ። 11 የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፣ የባሳንን ንጉሥ ዐግን፣ የከነዓንን ነገሥታት ሁሉ ገደለ፤ 12 ምድራቸውንም ርስት አድርጎ፣ ለሕዝቡ ርስት እንዲሆን ለእስራኤል ሰጠ። 13 እግዚአብሔር ሆይ፤ ስምህ ዘላለማዊ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ መታሰቢያህም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። 14 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳልና፣ ለአገልጋዮቹም ይራራላቸዋል። 15 የአሕዛብ ጣዖታት ከብርና ከወርቅ የተሠሩ፣ የሰው እጅ ያበጃቸው ናቸው። 16 አፍ አላቸው፤ አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው፤ አያዩም፤ 17 ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም፤ በአፋቸውም እስትንፋስ የለም። 18 እነዚህን የሚያበጁ፣ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ። 19 የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኩ፤ የአሮን ቤት ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኩ፤ 20 የሌዊ ቤት ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኩ፤ እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኩ። 21 በኢየሩሳሌም የሚኖር እግዚአብሔር፣ ከጽዮን ይባረክ። ሃሌ ሉያ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.