ዘኍል 33 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምእስራኤላውያን ከግብጽ እስከ ሞዓብ ሲጓዙ የሰፈሩባቸው ቦታዎች 1 እስራኤላውያን በየነገዳቸው ተከፋፍለው በሙሴና በአሮን መሪነት ከግብጽ ወጥተው፣ በጕዞ ላይ ሳሉ የሰፈሩባቸው ቦታዎች እነዚህ ናቸው፤ 2 ሙሴም በጕዟቸው ላይ ሳሉ የሰፈሩባቸውን ቦታዎች በእግዚአብሔር ትእዛዝ መዘገበ፤ በየቦታው እየሰፈሩ ያደረጉት ጕዞም ይህ ነው፦ 3 እስራኤላውያን በመጀመሪያው ወር በዐሥራ ዐምስተኛውም ቀን በፋሲካ ማግስት ከራምሴ ተነሡ፤ ግብጻውያን ሁሉ እያዩአቸውም በልበ ሙሉነት ተጓዙ። 4 በዚህ ጊዜ ግብጻውያን እግዚአብሔር ከመካከላቸው የገደለባቸውን በኵሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ እግዚአብሔር በግብጽ አማልክት ላይ ፈርዶ ነበርና። 5 እስራኤላውያን ከራምሴ ተነሥተው በሱኮት ሰፈሩ። 6 ከሱኮትም ተነሥተው በምድረ በዳው ዳርቻ በምትገኘው በኤታም ሰፈሩ። 7 ከኤታም ተነሥተው ከበኣልዛፎን በስተምሥራቅ ወዳለችው ወደ ፊሀሒሮት በመመለስ በሚግዶል አጠገብ ሰፈሩ። 8 ከፊሃሒሮት ተነሥተው በባሕሩ ውስጥ በማለፍ ወደ ምድረ በዳው ሄዱ፤ ከዚያም በኤታም ምድረ በዳ ሦስት ቀን ተጕዘው በማራ ሰፈሩ። 9 ከማራ ተነሥተው ዐሥራ ሁለት የውሃ ምንጮችና ሰባ የተምር ዛፎች ወደ ነበሩበት ወደ ኤሊም መጥተው በዚያ ሰፈሩ። 10 ከኤሊም ተነሥተው በቀይ ባሕር አጠገብ ሰፈሩ። 11 ከቀይ ባሕር ተነሥተው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ። 12 ከሲና ምድረ በዳ ተነሥተው በራፍቃ ሰፈሩ። 13 ከራፍቃ ተነሥተው በኤሉስ ሰፈሩ። 14 ከኤሉስ ተነሥተው በራፊዲም ሰፈሩ፤ በዚያም ሕዝቡ የሚጠጣው ውሃ አልነበረም። 15 ከራፊዲም ተነሥተው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ። 16 ከሲና ምድረ በዳ ተነሥተው በቂብሮት ሃታአባ ሰፈሩ። 17 ከቂብሮት ሃታአባ ተነሥተው በሐጼሮት ሰፈሩ። 18 ከሐጼሮት ተነሥተው በሪትማ ሰፈሩ። 19 ከሪትማ ተነሥተው በሬሞን ዘፋሬስ ሰፈሩ። 20 ከሬሞን ዘፋሬስ ተነሥተው በልብና ሰፈሩ። 21 ከልብና ተነሥተው በሪሳ ሰፈሩ። 22 ከሪሳ ተነሥተው በቀሄላታ ሰፈሩ። 23 ከቀሄላታ ተነሥተው በሻፍር ተራራ ሰፈሩ። 24 ከሻፍር ተራራ ተነሥተው በሐራዳ ሰፈሩ። 25 ከሐራዳ ተነሥተው በማቅሄሎት ሰፈሩ። 26 ከማቅሄሎት ተነሥተው በታሐት ሰፈሩ። 27 ከታሐት ተነሥተው በታራ ሰፈሩ። 28 ከታራ ተነሥተው በሚትቃ ሰፈሩ። 29 ከሚትቃ ተነሥተው በሐሽሞና ሰፈሩ። 30 ከሐሽሞና ተነሥተው በምሴሮት ሰፈሩ። 31 ከምሴሮት ተነሥተው በብኔያዕቃን ሰፈሩ። 32 ከብኔያዕቃን ተነሥተው በሖርሃጊድጋድ ሰፈሩ። 33 ከሖርሃጊድጋድም ተነሥተው በዮጥባታ ሰፈሩ። 34 ከዮጥባታ ተነሥተው በዔብሮና ሰፈሩ። 35 ከዔብሮና ተነሥተው በዔጽዮንጋብር ሰፈሩ። 36 ከዔጽዮንጋብር ተነሥተው በጺን ምድረ በዳ ባለችው በቃዴስ ሰፈሩ። 37 ከቃዴስ ተነሥተው በኤዶም ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ ሰፈሩ። 38 በእግዚአብሔር ትእዛዝ ካህኑ አሮን ወደ ሖር ተራራ ወጣ፤ እዚያም እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ በአርባኛው ዓመት፣ በዐምስተኛው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሞተ። 39 አሮን በሖር ተራራ ላይ ሲሞት፣ ዕድሜው መቶ ሃያ ሦስት ዓመት ነበር። 40 በከነዓን በምትገኘው በኔጌብ የሚኖረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ፣ የእስራኤላውያንን መምጣት ሰማ። 41 እነርሱም ከሖር ተራራ ተነሥተው በሴልሞና ሰፈሩ። 42 ከሴልሞና ተነሥተው በፋኖን ሰፈሩ። 43 ከፋኖን ተነሥተው በአቦት ሰፈሩ። 44 ከአቦት ተነሥተው በሞዓብ ዳርቻ በምትገኘው በዒዮዓባሪም ሰፈሩ። 45 ከጋይም ተነሥተው በዲቦንጋድ ሰፈሩ። 46 ከዲቦንጋድ ተነሥተው በዓልሞን ዲብላታይም ሰፈሩ። 47 ከዓልሞን ዲብላታይም ተነሥተው በናባው አጠገብ በሚገኙት በዓባሪም ተራሮች ላይ ሰፈሩ። 48 ከዓባሪም ተራሮች ተነሥተው ከኢያሪኮ ማዶ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ባለው በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፈሩ። 49 እዚያም በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ በሞዓብ ሜዳ ከቤትየሺሞት እስከ አቤልስጢም ባለው ስፍራ ሰፈሩ። 50 ከኢያሪኮ ማዶ በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው በሞዓብ ሜዳ፣ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 51 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ወደ ከነዓን ለመግባት ዮርዳኖስን ስትሻገሩ፣ 52 የምድሪቱን ነዋሪዎች በሙሉ ከፊታችሁ አሳድዳችሁ አስወጧቸው፤ የተቀረጹ ምስሎቻቸውንና ቀልጠው የተሠሩ ጣዖቶቻቸውን በሙሉ አጥፉ፤ እንዲሁም በኰረብታ ላይ የተሠሩትን መስገጃዎቻቸውን ሁሉ አፈራርሱ። 53 ምድሪቱን ርስት አድርጌ ሰጥቻችኋለሁና ውረሷት፤ ኑሩባትም። 54 ምድሪቱንም በየጐሣዎቻችሁ በዕጣ ተከፋፈሉ። ከፍ ያለ ቍጥር ላለው ሰፋ ያለውን፣ ዝቅተኛ ቍጥር ላለው ደግሞ አነስተኛውን ስጡ፤ ምንም ይሁን ምን በዕጣ የወጣላቸው፣ የየራሳቸው ርስት ይሆናል። አከፋፈሉም በየአባቶቻችሁ ነገዶች አንጻር ይሁን። 55 “ ‘የምድሪቱን ነዋሪዎች አሳድዳችሁ ሳታስወጧቸው ብትቀሩ ግን፣ እንዲኖሩ የተዋችኋቸው ሰዎች ለዐይናችሁ ስንጥር፣ ለጐናችሁም እሾኽ ይሆኑባችኋል፤ በምትኖሩበትም ምድር ችግር ይፈጥሩባችኋል። 56 እኔም በእነርሱ ላይ ለማድረግ ያሰብሁትን በእናንተ ላይ አደርግባችኋለሁ።’ ” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.