Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዮናስ 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ዮናስ እግዚአብሔር ምሕረት በማድረጉ ተቈጣ

1 ዮናስ ግን ፈጽሞ አልተደሰተም፤ ስለዚህም ተቈጣ።

2 ወደ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁትስ ይህን አልነበረምን? ፈጥኜ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል የተነሣሁትም ለዚሁ ነበር፤ አንተ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣ የዘገየህ አምላክ፣ ምሕረትህ የበዛ፣ ጥፋትንም ከማምጣት የምትመለስ እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ።

3 አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ ነፍሴን ውሰድ፤ ከመኖር መሞት ይሻለኛልና።”

4 እግዚአብሔር ግን፣ “በውኑ ልትቈጣ ይገባሃልን?” አለው።

5 ዮናስም ከከተማዪቱ ወጥቶ በስተምሥራቅ በአንድ ስፍራ ተቀመጠ። በዚያም ለራሱ ዳስ ሠራ፤ በከተማዪቱም የሚሆነውን ለማየት ከዳሱ ጥላ ሥር ተቀመጠ።

6 እግዚአብሔር አምላክም የቅል ተክል አብቅሎ፣ የዮናስ ራስ ጥላ እንዲያገኝና ሙቀትም እንዳያስጨንቀው ከበላዩ እንዲያድግ አደረገ፣ ዮናስም ስለ ቅሉ እጅግ ደስ አለው።

7 ነገር ግን በሚቀጥለው ቀን በማለዳ እግዚአብሔር ትል አመጣ፤ ትሉም ቅሉን በላ፤ ቅሉም ደረቀ።

8 ፀሓይ ስትወጣ፣ እግዚአብሔር የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ አመጣ፤ ፀሓዩም የዮናስን ራስ አቃጠለ፤ እርሱም ተዝለፈለፈ፤ መሞትም ፈልጎ፣ “ከመኖር መሞት ይሻለኛል” አለ።

9 እግዚአብሔር ግን ዮናስን፣ “በውኑ ስለ ቅሉ ልትቈጣ ይገባሃልን?” አለው። እርሱም፣ “በርግጥ እስከ ሞት ልቈጣ ይገባኛል” አለ።

10 እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለው፤ “አንተ እንዲበቅል ወይም እንዲያድግ ላልደከምህበት ለዚህ ቅል እጅግ ዐዝነሃል፤ በአንድ ሌሊት በቀለ፤ በአንድ ሌሊትም ደረቀ።

11 ታዲያ፣ እኔ ቀኝና ግራቸውን ለይተው መናገር የማይችሉ፣ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሰዎችና አያሌ እንስሳት ለሚኖሩባት ለታላቋ ከተማ ለነነዌ ማዘን አይገባኝምን?”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Siga-nos em:



Anúncios