Biblia Todo Logo
A Bíblia On-line

- Anúncios -


ዮናስ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የዮናስ ጸሎት

1 ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤

2 እንዲህም አለ፤ “ተጨንቄ ሳለሁ ወደ እግዚአብሔር ተጣራሁ፤ እርሱም መለሰልኝ፤ ከመቃብሩም ጥልቅ ርዳታን ፈልጌ ተጣራሁ፤ አንተም ጩኸቴን ሰማህ።

3 ጥልቅ ወደ ሆነው፣ ወደ ባሕሩ መካከል ጣልኸኝ፤ ፈሳሾችም ዙሪያዬን ከበቡኝ፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ፣ በላዬ ዐለፉ።

4 እኔም፣ ‘ከፊትህ ጠፋሁ፣ ነገር ግን እንደ ገና፣ ወደ ቅዱስ መቅደስህ፣ እመለከታለሁ’ አልሁ።

5 ውሃ እስከ ዐንገቴ አጠለቀኝ፤ ጥልቁም ከበበኝ፤ የባሕርም ዐረም በራሴ ላይ ተጠመጠመ።

6 ወደ ተራሮች መሠረት ሰመጥሁ፤ የምድርም በር ለዘላለም ተዘጋብኝ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ ግን ሕይወቴን ከጕድጓድ አወጣህ።

7 “ነፍሴ በዛለች ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን ዐሰብሁ፤ ጸሎቴም ወደ አንተ፣ ወደ ቅዱስ መቅደስህ ዐረገች።

8 “ከንቱ በሆኑ ጣዖቶች ላይ የሚንጠለጠሉ፣ ሊያገኙ የሚገባቸውን ጸጋ ያጣሉ።

9 እኔ ግን በምስጋና መዝሙር፣ መሥዋዕት እሠዋልሃለሁ፤ የተሳልሁትንም እሰጣለሁ፤ ‘ድነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።’ ”

10 እግዚአብሔርም ዓሣውን አዘዘው፤ ዮናስንም በደረቅ ምድር ላይ ተፋው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Siga-nos em:



Anúncios